August 3, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የዛሬው ችግኝ ተከላ ለወደፊቷ የበለፀገች ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው፡- አቶ አደም ፋራህ

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ውጥን አካል በሆነው የታሪክ ሁነት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሀገራችን ዘርፈ ብዙና ዘላቂ ጥቅሞችን ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በመገኘት አሻራቸውን ያኖሩት አቶ አደም ፋራህ፣ የዛሬው መርሐ ግብር ባለፈው ዓመት የተመዘገበውን የራሳችንን ክብረ ወሰን የሚያሻሽልና ለወደፊቷ የበለፀገች ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስገኛቸውን ዋና ዋና ጥቅሞች በሦስት ዐበይት ዘርፎች ከፍለው አብራርተዋል።

የመጀመሪያው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ማፋጠኑ ሲሆን፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተተከሉ 48 ቢሊዮን ችግኞች የሥነ-ምህዳር ደህንነት መጠበቁን፣ የአፈር መሸርሸር መከላከል መቻሉን፣ የውኃ አካላት መታደሳቸውንና የግብርና ምርታማነት ማደጉን አመልክተዋል።

በተለይም እንደ አቮካዶና ቡና ያሉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ችግኞች በመትከል የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከመጨመሩ ባሻገር፣ ከውጭ ይገቡ የነበሩ እንደ ስንዴ ያሉ መሰረታዊ ሰብሎችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በመተካት የምግብ ዋስትናን፣ የኢኮኖሚና የሀገር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መቻሉን አስረድተዋል።

ሁለተኛው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው በጋራ በመሳተፋቸው ማህበራዊ ካፒታልና የወንድማማችነት እሴት እንዲጎለብት በማድረግ የሀገር ግንባታ ሂደቱን ማፋጠኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሀገራችን በተግባር ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ በመስጠት ረገድ ያሳየችውን ተምሳሌትነት በመጥቀስ፣ በተፈጠረው የዲፕሎማሲ አቅም ኢትዮጵያ የኮፕ 32 (COP32) ጉባኤን ለማዘጋጀት ዕድል ማግኘቷን አብራርተዋል።

አቶ አደም ፋራህ በቀጣይም ይህን መርሃ ግብር አጠናክሮ በመቀጠል የተገኙትን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አዝልቆ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

#EBC