August 26, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የባህር በር – የኢትዮጵያ የፍትህና የልማት ጥያቄ

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከማናቸውም የዕለት ተዕለት የፖለቲካ ትኩሳትና ፉክክር የጸዳ፤ መነሻው ከታሪክ እውነታ፣ ከዓለም አቀፍ ሕግ፣ ከፍትሃዊነት እንዲሁም ከአንዲት ጥንታዊት ሀገር ሁለንተናዊ ህልውና የሚመነጭ የመልማት የመበልጸግ ጥያቄ ነው።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የባህር በር የነበራትና ከቀይ ባህር ጂኦፖለቲካዊ ትስስር ጋር በጥብቅ የተቆራኘች ሀገር ሆና ሳለ፣ ህዝብ ባልመረጣቸው የቀድሞ ፖለቲከኞች ታሪካዊ ሴራ የባህር በር አልባ ተደርጋለች።

በመሆኑም ዛሬ ላይ የባህር በር ባለቤትነትን በተመለከተ የሚደረገው ማንኛውም ጥረት፣ የቅንጦት ሳይሆን በታሪክ የተዛባን ፍትህ የማቅናትና የነገውን ትውልድ ህልውና እና ሉዓላዊ ደህንነት የማረጋገጥ ግዴታ ነው።

ከ130 ሚሊየን በላይ የሆነ ግዙፍ የህዝብ ቁጥር ያላትና በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ የምታስመዘግብ ሀገር፣ ፍትህ ተጓድሎ ከባህር በር እንድርቅና ተዘግቶባት እንድትቀር ማድረግ ታሪካዊ በደል ነው።

የባህር በር ማግኘትም ሆነ መጠቀም በዓለም አቀፍ የባህር ሕግ መሠረት የተረጋገጠ መብትና ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ጥያቄ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ስልታዊና ሰፊ የጂኦግራፊ አቀማመጥ፣ እንዲሁም ከምትጫወተው የሰላም ማስከበርና በጋራ የመልማት ሚና አኳያ፣ በርካታ ዓለም አቀፍ ኃይሎች በትኩረት በሚከታተሉት የቀይ ባህር ቀጣና ዳር ቆማ ተመልካች ልትሆን ፈጽሞ አትችልም።

የመደመር መንግሥት ይህንን ብሔራዊ ጥያቄ በይፋና ወደ አደባባይ ሲያመጣው፣ በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ጥረት፣ በጠንካራ የንግድ ትስስር እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ የሰለጠነ መርህ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄያ ጊዜያዊ አጀንዳ ሳይሆን ለመጻኢው የኢትዮጵያ ጊዜ ብሩህ ተስፋን ያዘለ በመሆኑ፣ ስኬታማነቱን በተግባር ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የማያወላውል ድጋፍና ትብብር እጅግ ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ በሰላምና በዲፕሎማሲ መንገድ የባህር በር ባለቤትነቷን ማረጋገጧ ለራሷ የብልጽግና ጉዞ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ቀጣናው የጋራ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም የማይተካ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል።

(ኤፍ ኤም ሲ)