September 8, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የፅናት ቀንን የምናከብረዉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለዘመናት ያፀኑ ጀግኖችን ዕውቅና ለመስጠት፤ የዛሬ ጀግኖችን ለማበረታታት እና የነገ ጀግኖችን ለመፍጠር ነው-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የፅናት ቀንን የምናከብረዉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለዘመናት ያፀኑ ጀግኖችን ዕውቅና ለመስጠት፤ የዛሬ ጀግኖችን ለማበረታታት እና የነገ ጀግኖችን ለመፍጠር ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን 3 የፅናት ቀንን በማስመልከት ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ፅናት የኢትዮጵያውያን የትናንትም የዛሬም መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን የጋራ ዐጥንት እና ደም ተጠብቃ የቆየች የኩራት እና ክብር ምንጭ ናት፡፡ ለዚህም ነው ከትናንት እስከ ዛሬ ከየትኛዉም አቅጣጫ፣ በማንኛዉም ኃይል የሚቃጡ ጥቃቶችን ኹሉ በጀግንነት መመከት፣ ነፃ እና ሉዓላዊ ሀገር ለትውልድ ማስረከብ የተቻለው፡፡

ጳጒሜን 3 ቀንን የፅናት ቀን በሚል ስያሜ የምናከብረዉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለዘመናት ያፀኑ ጀግኖችን ዕውቅና ለመስጠት፤ የዛሬ ጀግኖችን ለማበረታታት እና የነገ ጀግኖችን ለመፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር ግንባሮች ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ ፅኑ ጀግኖችን አፍርታለች፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም ፈር በቀደደዉ የሥነ መንግሥት ታሪኳ ከጠላት ትንኮሳ የተላቀቀችበት ዘመን አልነበረም፡፡ ጡንቻዋ ሲፈረጥም ታፍራ እና ተከብራ፤ የሟሸሸ ሲመስል ደግሞ ለጥቃት ተጋልጣ ታውቃለች፡፡

ያለስስት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ዋጋ የሚከፍሉ ልጆቿም ዘወትር ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር በተጠንቀቅ ይጠብቋታል፡፡ የጠላቶቿ ሴራ እና ትንኮሳም የበለጠ አጠንክሯት እና ጀግንነቷን ፈልቅቆ አውጥቶት እንጅ ሉዓላዊነቷን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶት አያውቅም፡፡

ኢትዮጵያውን በጋራ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በየጊዜዉ ወታደራዊ ጥበብን ተላብሰው፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ነፃነት ዋጋ እየከፈሉ ከዚህ ዘመን ደርሰዋል፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን ሰብእና፣ ወታደራዊ ዲስፕሊን እና ሥልጠናም በበቂ ተላብሰዋል፡፡ ጠላት ከትንኮሳ በፊት ደጋግሞ እንዲያስብ የሚያስገድድ ሰብአዊ ልማት እና የቴክኖሎጂ ዐቅም ተፈጥሯል፡፡

በየግንባሩ የተገነባዉ ሠራዊት ከኢትዮጵያ የብልጽግና ትልም ፊት ለመቆም የሚውተረተር ደንቃራን ኹሉ የማጽዳት፤ የተረከባትን ነፃ ሀገር በነፃነት ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ፣ ኢትዮጵያ መሻቷን ኹሉ በግዛቷ ውስጥ በነፃነት የማድረግ ዐቅም እንዲኖራት የማገዝ ተልእኮን ያነገበ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚሹ ጠላቶች ነበሩ፤ ይኖራሉም፡፡ ነገር ግን በሠራዊታችን የማድረግ ዐቅም ማደግ፤ በተገነባበት የማሸነፍ ሥነ ልቦና እና በታጠቀዉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በተካሄደዉ አካታች ሀገራዊ ምክክር የተላላኪ ባንዳዎች የማኩረፊያ ቀዳዳ መደፈን የጠላት የማድረግ ዐቅም ከሐሳብ የማይሻገርበት ኹኔታ ተፈጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የፖለቲካ ቅራኔ ያላቸው ኹሉ አኩርፈው ጫካ የሚገቡባት እና የጠላት መጠቀሚያ የሚኾኑባት ሀገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የሚያሳሳ ነገን እየገነባች፤ በወል እውነት ላይ የጸናች፤ ብዝኃነትን ጌጥ ያደረገ ሕዝባዊ ሠራዊት ያላት፣ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ለመኾን ወደ ከፍታ እየተስፈነጠረች ያለች ሀገር ናት፡፡ ከዚህ ጉዞዋ ሊያደናቅፋት የሚሻን መሰናክል ኹሉ ደጋግሞ እንዲያስብ፣ የአየር፣ የባሕር እና የሳይበር ተቋም እና ሠራዊት ገንብታለች፡፡

በዛሬው ዕለት የፅናት ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ነፃነት ለማስከበር፣ ለሕዝቦቿ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ መሥዋዕትነት የከፈሉ እና እየከፈሉ ያሉ ጀግኖችን በማክበር እና ዐሻራቸዉን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቃል በመግባት ነው፡፡

ጳጒሜን 03 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት