የግጭትን መንገድ ትቶ ወደ ሰላማዊ ውይይት በመምጣት በአንድ መድረክ ላይ በእጃቸው መሳሪያ ሳይሆን ብዕርን በመያዝ ሀሳባቸውን ለማስፈር መላው ኢትዮጵያውያን ተገናኝተዋል።
የሀገር ግንባታ መሠረቱ የሚጠነክረው በግጭት ሳይሆን በመደማመጥ፣ እንዲሁም በጋራ በሚገነባ የሀሳብ ራዕይ መሆኑን በማስረፅ።
በዚህ እሳቤ መሠረት ነው የሀገራዊ ምክክር ሂደት “የሁሉም ሀሳብ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል” በሚል መርህ የሁሉንም ድምፅ ለማዳመጥ በር የከፈተው።
ሀገራዊ ምክክር ዓላማው ልክ እንደ ውድድር አሸናፊና ተሸናፊ መለየት ሳይሆን በሕዝቦች ዘንድ የተወከሉ ተወካዮች ተጠናክረው የጋራ መፍትሔ በመፈለግ በሁሉም ውስጥ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ነው።
ለዚህም ዋና ማሳያ የሆነው ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች በስምንት ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ በቡድን ተከፋፍለው እየተወያዩ ይገኛሉ።
ዓመታትን በትጥቅ ትግል ያሳለፉ ተመካካሪዎች ዛሬ መሣሪያን አስቀምጠው ብዕር በመያዝ ሐሳባቸውን በውይይት እያቀረቡ ይገኛሉ፤ ይህ የሚጠቁመው ምልክት የጦርነትን ኃይል ሳይሆን በመመካከር ችግሮች ሊፈቱ እንደሚችሉ የሚያሳይ ተስፋ ሰጪ ምልክት እና የሰላም መንገድ ለሁሉም ክፍት መሆኑን ያረጋግጣል።
ተመካካሪዎቹ ከ250 አባላት ወደ 50 አባላት፣ በመጨረሻም ወደ 10 አባላት በመከፋፈል ሁሉም ተመካካሪ ያመጣውን የማኅበረሰብ ጥያቄና ሐሳብ ያለ ግፊት፣ ያለ ፍርሃት እና ያለ ተፅዕኖ በነፃነት እንዲያቀርብ ዕድል ተፈጥሮለታል።
ልዩነታቸው ውበታቸው የሆነው የኢትዮጵያውያን ሐሳቦች ሲገናኙ፣ ልዩነቶች ሲከበሩ እና ሁሉም ድምፅ የመደመጥ ዕድል ሲያገኝ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ በተስፋ እና በመተማመን የተመሠረተች ትሆናለች። ለዘመናት የቆዩ ቁርሾዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የሰላም ባህልን ማጠናከር የዚህ ሂደት ትልቁ ስኬት ነው።
በዚህ መድረክ ላይ የሚጻፉት ቃላት በወረቀት ላይ ብቻ አይቀሩም፤ ወደ ታሪክ በመሻገር ከአዳራሹ አልፈው የቀጣዮቹን ትውልዶች ሊመሩ የሚችሉ እና ተስፋን፣ ይቅርታን፣ የጋራ ራዕይን የሚተክሉ ናቸው።
በዚህም ሀገር የምትገነባው በዜጎቿ የተረጋጋ ውይይት በመሆኑ ወደ ምክክር መምጣት የድክመት ምልክት ሳይሆን የብስለት፣ የኃላፊነት እና የጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታን በሰላማዊ መንገድ ለመወሰን የተወሰደ ጠንካራ እርምጃ ነው።
መሣሪያን በብዕር የተኩ እጆች የሚጽፉት የአንድ ቡድን ታሪክ አይደለም፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ የወደፊት ምዕራፍን ነው።
#EBC
More Stories
በሀገር አቀፍ ፈተና ላይ ብቁ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ:
የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተሰነዘረውን የጥቃት ሙከራ ተከትሎ ዋሽንግተን ኢራን ላይ “ከፍተኛ” ጥቃት ፈጸመች
ከማሻ ደገሌ መንገድ በእጅጉ በመበላሸቱ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ችግር እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ