የሰው ሰራሽ አስተውሎት አልሚ ድርጅት ኦፕን ኤአይ (OpenAI)፣ የፈጠራቸው የሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት ሞዴሎች የተቀመጠላቸውን የደህንነት ገደብ ጥሰው በመውጣት በራሳቸው ተነሳሽነት የሳይበር ጥቃት መሰንዘራቸውን ይፋ አደረገ።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ፣ ክስተቱ የተመዘገበው “ExploitGym” የተባለ የኤአይ ሞዴሎችን የደህንነት ብቃት የመፈተሻ ሙከራ በሚከናወንበት ወቅት ነው። የኤአይ ሞዴሎቹ ደህንነቱ በተጠበቀ እና ከሌሎች የኮምፒውተር መረቦች በተለየ የሙከራ ክልል ውስጥ እንዲቆዩ ቢደረግም፣ ሞዴሎቹ ይህንን የደህንነት አጥር በመስበር ወደ ውጭ መውጣት ችለዋል።
ድርጅቱ ባወጣው ዝርዝር መግለጫ፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነው የኤአይ ሞዴል “Hugging Face” የተባለውን የቴክኖሎጂ ተቋም የመረጃ መሠረተ ልማት ዒላማ በማድረግ ጥቃት ሰንዝሯል። ይህ ጥቃት የተፈጸመው ያለምንም የሰው ልጅ ትዕዛዝ፣ ግፊት ወይም ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በኤአዩ የራሱ ውሳኔ እና ተነሳሽነት መሆኑ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል።
ኦፕን ኤአይ ክስተቱን ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሲል የገለጸው ሲሆን፣ ኤአዩ በሌላ ተቋም ሲስተም ውስጥ ያሉ የደህንነት ክፍተቶችን በራሱ የመለየት እና ጥቃት የመሰንዘር ከፍተኛ ብቃት ማሳየቱን አረጋግጧል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆነው ሀጊንግ ፌስ በበኩሉ፣ “ኤአይ በራሱ ተነሳሽነት ጥቃት የመሰንዘር አቅም አለው የሚለው ስጋት አሁን በንድፈ-ሐሳብ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በተግባር የታየ እውነታ ሆኗል” ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ይህ አጋጣሚ በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፣ የኤአይ ቴክኖሎጂዎች የሰው ልጅን ቁጥጥር ሽሽት በማድረግ ሊያደርሱ የሚችሉትን የሳይበር ደህንነት አደጋ ዳግም አጀንዳ አድርጎታል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ይህ ክስተት ወደፊት በኤአይ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደረገው የደህንነት ቁጥጥር እና የሥነ-ምግባር ገደብ እጅግ ጥብቅ ሊሆን እንደሚገባ ማሳያ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኦፕን ኤአይ መሰል የደህንነት ጥሰቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የቁጥጥር ሥርዓቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየገመገመ መሆኑን አስታውቋል።
More Stories
አሜሪካ በኢራን ጦርነት ከ37 ቢሊየን ዶላር በላይ እንዳወጣች ተገለፀ::
ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግደው ሕግ በፈረንሳይ ምክር ቤት ጸደቀ።
የአፍሪካ እና የባህረ ሰላጤው (ገልፍ) የኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ መካሄድ ጀመረ