በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
አቶ ሰለሞን ከኢቲቪ ወቅታዊ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ይህ የምክክር ሂደት ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካ ጥያቄዎችንና የፖሊሲ አማራጮችን በአጀንዳነት ይዞ የቀረበ ድንቅ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ቀደም ሲል ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያነሱ የነበሩ አካላት አሁንም በተቃውሞ ብቻ መቆየታቸው ለሀገር አዋጭ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ የሀገርን ሰላምና የጋራ ራዕይ ለማስቀደም ወደ መድረኩ መምጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ የምክክር ሂደቱን ለማሳካት ባደረገው ርብርብና ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ዛሬ ላይ የበርካታ ፓርቲዎችንና ወደ 4,000 የሚጠጉ ተሳታፊዎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ መቻሉ ለዲሞክራሲና የውይይት ባህል ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አብራርተዋል።
ፖለቲካ ማለት ሁልጊዜ በመቃወም መኖር ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ሰብሳቢው፣ የግል ፍላጎትን በመተው በሐሳብ የበላይነት መወያየትና የሀገርን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ በክልሎች ያካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ግልጽነትና አሳታፊነት የታየበት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ገለልተኛነቱን ጠብቆ ሥራውን እንዲያከናውን ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል ብለዋል።
ሕዝቡ እውነተኛ መረጃዎችን እንዲያገኝ ሚዲያዎችም ሂደቱን በግልጽነት የመዘገብ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
EBC
More Stories
አሜሪካ በኢራን ጦርነት ከ37 ቢሊየን ዶላር በላይ እንዳወጣች ተገለፀ::
ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግደው ሕግ በፈረንሳይ ምክር ቤት ጸደቀ።
የአፍሪካ እና የባህረ ሰላጤው (ገልፍ) የኢኮኖሚያዊ ትብብር መድረክ መካሄድ ጀመረ