የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር ከሚያስችሉ ጉዳዮች ውስጥ ዘመኑን የዋጀ አየር ሃይል መገንባት ዋነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡
አየር ሃይል የአንድን ሀገር የአየር ክልል በንቃትና በተጠንቀቅ ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነም አስፈላጊውን አጸፋዊ ርምጃ በመውሰድ ጥቃቱን ይቀለብሳል ፤ፈጥኖም በአነስተኛ ኪሳራ ያጠናቅቃል፡፡
ለዚህ ደግሞ ዘመኑን የዋጀ እና ዓለም የደረሰችበትን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ አየር ሃይል መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡
የመደመር መንግሥት ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበና በሁለንተናዊ አቅሙ የጎለበተ ዘመናዊ አየር ሃይል ከመገንባት አንጻር ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች ናቸው፡፡
በዚህም የአየር ሃይሉን የቴክኖሎጂ ሽግግር በማጠናከር ቀጣናዊ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ አህጉራዊ ተወዳዳሪ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም የዘመኑን ውጊያ ስልት አጢኖ የሚረዳ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም ውጊያ ጨራሽ የሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ሌሎች ተዋጊ ጀቶች መታጠቅ ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመት በፊት የመረቁት ለሲቪልና ወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሚያመርተውን ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ መጥቀስ ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ ድሮን ስለማምረት ማሰብ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በእርግጥ ዘርፈ ብዙ ችሎታ ያላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በራስ አቅም በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ዲዛይን አድርጎ የማምረት አቅም መፍጠር ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው፡፡
ቴክኖሎጂው የጠላት እንቅስቃሴዎችን በቅጽበት ለመከታተል፣ ጥናት ለማድረግ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
መሰል አቅምን ይበልጥ ማጠናከርም አየር ሃይል ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ለመታጠቅ የጀመረውን ጥረት ይበልጥ ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በተለይም የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚረዳ የሰው ሃብት፣ ዘመናዊ ትጥቆችና የውጊያ መሰረተ ልማት ለማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
አየር ሃይል ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ጥቃቱን በአጭር ጊዜ ለመቀልበስና በትንሽ ኪሳራ ለመጨረስ ከማስቻሉ ባለፈ ግጭትን የማስቀረት አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
የቀጣናው የጸጥታ ሁኔታ በየጊዜው በፍጥነት በሚለዋወጥበት ሁኔታ እንዲሁም ግጭትን በሚፈልጉ ተዋንያን ፊት ግጭትን ለማስቀረት የሚችል አቅም መፍጠር ደግሞ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡
የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ እንደሚሉት÷ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገሪቷን አየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅና መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል፡፡
አየር ኃይሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂን በማፍለቅና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በ2022 ዓ.ም ከአፍሪካ ቀዳሚ የአየር ኃይል ለመሆን በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡
ለዚህም የለውጡ መንግሥት የአየር ሃይል አባላት ከፖለቲካና ከብሔር አስተሳሰብ እንዲወጡ በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሠራዊቱ በየቀኑ የመሳሪያ፣ የአካልና የእውቀት ፍተሻ በማድረግ የተሟላ ሥነ ልቦና ተላብሶ ሀገሩን እንዲጠብቅ እየተሰራ ነው፡፡
በሌላ በኩል አየር ሃይሉ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎችና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር በአቪዬሽን፣ በኤሮስፔስ ምህንድስና እና በዘመናዊ ኮሙኒኬሽን ላይ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያን ሰማይ ከማንኛውም ያልተፈቀደ እንቅስቃሴ ለመጠበቅና ሉዓላዊ ደህንነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ዘመናዊ የራዳር እና የዲጂታል ኮሙኒኬሽን ሥርዓቶች ተዘርግተው 24 ሰዓት በንቃት እየተቆጣጠሩ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ጦርነት በየትኛውም ሁኔታ ሊያጋጥም እና ሀገር ሊያፈርስ ይችላል ፤ ይህንን ለማስቀረት እንዲሁም ከተጀመረ አሳጥሮ ለመጨረስ ደግሞ አስተማማኝ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ስለሆነም የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በማወቅ ለማክሸፈና ለመመከት ጊዜውንና ነባራዊ ሁኔታውን የሚመጥን አየር ሃይል የመገንባት ሥራን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)
More Stories
የሕዝብ የጋራ ራዕይና የነገዋ ኢትዮጵያ ማሳያ፤ የሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎች ተስፋ ሰጪነት
መገናኛ ብዙሀን ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
አሜሪካ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እያወኩ ነው ባለቻቸው የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አዲስ ጥቃት ፈጸመች፡፡