ኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በስፋት ያሰባሰባቸው አጀንዳዎች፣ ሕዝቡ በአንድነትና በወንድማማችነት ለመኖር ያለውን የጸና ፍላጎት በግልጽ የሚያመላክቱ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት መምህር የሆኑት ተሻለ ተገኔ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አጀንዳዎች የፍላጎቶችን ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወዴት መሄድ እንዳለባትና አሁን ላይ ምን እንደሚጎድላት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
ሂደቱ እጅግ አሳታፊና ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ሐሳቡን በነፃነት ያቀረበበት መሆኑን ያመላከቱት መምህሩ፤ የቀረቡት ሐሳቦችም ብስለታቸውና ሀገራዊ አስፈላጊነታቸው በጥልቀት ታይቶ ለውይይት በሚመችና ማራኪ መንገድ በኮሚሽኑ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ደራሲና ጋዜጠኛ ጌታቸው ታደሰ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክር ማለት አንድ ጊዜ ተዘርቶ ወዲያው የሚታጨድ ፈጣን ክስተት ሳይሆን፣ ቀስ በቀስ ባህል እየሆነና እያደገ የሚሄድ ዘላቂ የሰላም ሂደት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ ሀገር ዘላቂ ተቀማጭነት ያለው እንዲህ ዓይነት ግዙፍ የውይይት መድረክ ተፈጥሮ እንደማያውቅ ያስታወሱት ደራሲው፤ ከተሰበሰቡት አጀንዳዎች መካከል አብዛኞቹ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባትና በሂደት ምላሽ የሚያገኙ እንጂ፣ ከምክክሩ መጠናቀቅ ማግስት ፈጣን ተአምራዊ ለውጥ የሚጠበቅባቸው እንዳልሆኑ ጠቁመዋል።
ይህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት አሁን ላይ ጠንካራ መሠረት መያዙንና በሕዝብ፣ በሀገር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዕውቅና ማግኘቱን አመላክተዋል።
የሂደቱ ዋና ባለቤት ራሱ ሕዝቡ በመሆኑ ወደፊትም በምክክር ኮሚሽኑም ሆነ በአስፈፃሚው የመንግሥት አካል ላይ ያቀረባቸውን ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ተከታታይ ጥያቄዎችንና ክትትሎችን ማድረጉን እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
More Stories
የኢትዮጵያን አየር ክልል በተጠንቀቅ የሚቃኘው አየር ሃይል …የሰማዩ ንስር
መገናኛ ብዙሀን ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል
አሜሪካ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እያወኩ ነው ባለቻቸው የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አዲስ ጥቃት ፈጸመች፡፡