ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላቸው 53ቱም የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የቡና ምርቶች ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ ገበያዋ እንዲገቡ እንደምትፈቅድ የቻይና ጉምሩክ አጠቃላይ አስተዳደር (GAC) አስታውቋል።
ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው የቡና ምርት፣ ከደረቀ ቃሪያ ቀጥሎ ሙሉ በሙሉ ወደ ቻይና ገበያ እንዲገባ የተፈቀደለት ሁለተኛው የአፍሪካ የግብርና ምርት ሆኗል።
በዚህ አዲስ አሠራር መሠረት ኢትዮጵያ እና ብሩንዲን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት ወደ ቻይና የሚላኩ የቡና ፍሬዎቻቸውን አስቀድመው ያረጋገጡ ሲሆን፣ ሞሪሸስ፣ አንጎላ፣ ቶጎ፣ ጊኒ፣ ላይቤሪያ እና ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ደግሞ የወጪ ንግድ ፈቃድ ማመልከቻቸውን አቅርበዋል።
የቻይና ጉምሩክ አጠቃላይ አስተዳደር በአፍሪካ የቡና አመራረት ሥርዓት እና የተባይ መከላከያ ሂደቶች ላይ ጥብቅ ግምገማ ካደረገ በኋላ ወጥ የሆነ የእፅዋት ጤና መስፈርት ያወጣ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም ከእያንዳንዱ ሀገር ጋር በተናጠል ይደረግ የነበረውን የኳራንቲን ድርድር እና የመዳረሻ ሂደት በእጅጉ እንደሚያቀላጥፈው ተገልጿል።
ሆኖም ወደ ቻይና ገበያ ሙሉ ተደራሽነት ማግኘት ማለት ከድንበር ፍተሻ ነፃ መሆን አለመሆኑን ያመለከቱት ባለሙያዎች፣ ሁሉም ማጓጓዣዎች በአውሮፖውያኑ 2026 ዓ.ም. በማስታወቂያ ቁጥር 68 የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የቻይና ባለስልጣናት በበኩላቸው “አረንጓዴ ቻናል” የተባለውን የማመቻቸት ሥርዓት ይበልጥ በማሻሻል፣ ከአፍሪካ የሚመጡ ጥራት ያላቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ የግብርና እና የምግብ ምርቶች ወደ ቻይና ገበያ እንዲገቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
More Stories
ዓመታዊ የወጪ ንግድ ያስገኘው ገቢ ጨምሯል ተባለ
አዲሱ የማዕድንና ኢንዱስትሪ ትስስር
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ የጀርባ አጥንት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው