የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፍሪካ ቀንድን በአረንጓዴ ልማት ለማስተሳሰር እና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እየተአሸጋግረውታል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመከላከል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በዋናነትም ለጅቡቲ፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለኬንያ አበርክታለች፡፡
ህዝባዊው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ፣ የደን ሽፋንን በመጨመር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያገለገለ ይገኛል፡፡
የአረንጓዴ አሻራን ከኢኮኖሚ ጥቅሞች ጋር ማቀናጀት በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን የግብርና ኤክስፖርት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል፡፡
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ለምግብነትና ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚውሉ የጥምር እርሻ ችግኞች ድርሻ 57 በመቶ ያህል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ያሉ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች በየዓመቱ ከሚዘጋጁት ችግኞች ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ።
እነዚህ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች አሁን ላይ ምርት በመስጠት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ተርፈው ወደ ውጪ ሀገራት መላክ ጀምረዋል፡፡
በአፍሪካ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ለረጅም ዓመታት በአቮካዶ ላኪነት የሚታወቁ ሀገራት ናቸው፡፡
ከአረንጓዴ አሻራ በፊት ምንም ድርሻ ያልነበራት ኢትዮጵያ አሁን ላይ በተሻሻሉ የሀስ የአቮካዶ ዝርያዎች አማካኝነት በፈጣን ዕድገት ላይ ትገኛለች፡፡ በቅርብ አመታት ውስጥም የቀዳሚነት ድርሻን ለመውሰድ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች የሀገሪቱን የግብርና መዋቅር ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ አሸጋግረውታል።
የተሻሻሉ የአቮካዶ፣ የማንጎ እና የፓፓያ ዝርያዎች በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምስራቅ ገበያዎች ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነትን አግኝተዋል።
ይህም የኢትዮጵያን የገበያ መዳረሻዎች እያሰፋው ነው፡፡
ይህ የፍራፍሬ ምርት ላኪነት ጅማሮ አነስተኛ አርሶ አደሮች ከባህላዊ ሰብል ምርት ወጥተው ከፍተኛ ገቢ ወደሚያስገኙ የፍራፍሬ ምርቶች እንዲሸጋገሩና የውጪ ምንዛሪ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
የፍራፍሬ ዛፎች መተከላቸው የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባለፈ፣ በተቀናጀ የግብርና ልማት አርሶ አደሩ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ትኩረት እየሰጠ የኢኮኖሚ ጥቅሙን እንዲያሳድግ አድርጎታል።
ፍራፍሬዎቹን በጥራት ወደ ውጪ ለመላክ የቀዝቃዛ ሰንሰለት የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች እና የማሸጊያ ኢንዱስትሪዎች በሀገሪቱ እንዲስፋፉ በር ከፍቷል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባለፈ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ያለውን ትልቅ አቅም በተግባር ያሳየ ስኬት ነው።
ይህ ተሞክሮ የአረንጓዴ ልማትና የምግብ ዋስትናን እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገትን ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚቻል ማረጋገጫ ሆኗል።
በቀጣይም የምርቶቹን ብዛትና ጥራት በማሳደግ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማዘመን እና አዳዲስ የውጪ ገበያዎችን በማሰስ ይህንን ስኬታማ ጉዞ ማስፋትና ማስቀጠል ያስፈልጋል።
More Stories
ከማሻ ደገሌ መንገድ በእጅጉ በመበላሸቱ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ችግር እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ
ከወጪ ንግድ 607 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ
በጅማ ዞን የተመረተ ከ6.7 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የአቮካዶ እና የሙዝ ምርት ለገበያ ቀረበ