August 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ያደሩ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር አዳዲሶቹን ጀምሮ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሸካ ዞን የኪ ወረዳ በቆ ቀበሌ የተገነባው የቦን ገጠር ሞዴል መንደር ተመርቋል።

የገጠር ሞዴር መንደሩን የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን መርቀው ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል።

በሸካ ዞን የኪ ወረዳ በቆ ቀበሌ የቦን ገጠር ሞዴል መንደሩ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ነው የተገነባው።

በምረቃ ወቅት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ብልፅግና ፓርቲ ያደሩ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር አዳዲሶቹን ጀምረው በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን የሰላም፣ ልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎችን ለመመለስ ባለው አቅም ተግባራትን አቀናጅተው በመምራት ክልሉን ለመቀየር በቁርጠኝነት ተግባራትን ሲፈጽም መቆየቱን ነው አቶ ፍቅሬ አማን የገለጹት።

የለውጡ መንግሥት የገጠሩን ማሕበረሰብ ኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንሼቲቭ ቀርጸው ተግባራዊ እያደረገ ካሉት ተግባራት መካከል የገጠር ሞዴል መንደር ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ኢንሼቲቩ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ በ16 ወረዳዎች የገጠር ሞዴል መንደር ግንባታ አስጀምረው በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የገጠር ሞዴል መንደር ዘመናዊ የሰዎች መኖሪያ ቤት፣ የሌማት ትሩፋት፣ ጓሮ አትክልትና ሌሎች መሠረታዊ መሠረተ ልማቶችን አቀናጅተው የያዘ በመሆኑ የነዋሪዎችን ኑሮ ከማዘመን ባለፈ ለሀብት መፍጠሪያ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው አቶ ፍቅሬ አማን የተናገሩት።

በመንግሥትና ፓርቲ የተጀመረው ኢንሼቲቭ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች እንዲጠናከር አርሶ አደሮችም ከስራው ልምድ በመውሰድ አከባቢያቸውን ሞዴል ለማድረግ እንዲሰሩ አሳስበው የክልሉ ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላቸው ጋራ የገጠር ሞዴል መንደሩ የገጠሩን ማሕበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ በማዘመን ምቹ አከባቢ ለመፍጠር ታስቦ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በወረዳው በቆ ቀበሌ የተገነባው የቦን ገጠር ሞዴል መንደር ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ መሆኑን የተናገሩት የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ ናቸው።

ለሥራው መሳካት በየደረጃው በገንዘብ፣ እውቀትና ጉልበት አስተዋጽኦ ላበረከቱ መዋቅሮችና አካላት ምስጋና አቅርበዋል የወረዳው አስተዳዳሪ።

በምረቃው የኢፊድሪ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታዎችን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።