July 11, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከክልሉ 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቧል‎

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በወርቅ ምርት እመርታዊ ውጤት መመዝገቡን መግለጻቸው ይታወሳል።

‎በዚህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከወርቅ ማዕድን ምርት 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማገኘት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በብዝሀ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማዕድን ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት ውጤቱን ከፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

‎የወርቅ ማዕድን ከሚመረትባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም ለዘርፉ በተሰጠ ትኩረት የወቅር ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።

‎ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ወልያብ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው የወርቅ አቅርቦት ምጣኔ ከፍተኛ ነው።

‎ለእዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 350 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ 348 ኪሎ ግራም ምርት መቅረቡን በማሳያነት ተናግረዋል።

‎አፈጻጸሙ በ2017 በጀት ዓመት ከክልሉ ከቀረበው 155 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት አንጻር ሲታይ በከፍተኛ መጠን ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

‎የለውጡ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ትኩረትና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ጠንካራ ክተትል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቁመዋል።

‎በ2019 በጀት ዓመትም ከዘንድሮ ከፍ ያለ የወርቅ መጠን ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ አቅምን በማጠናከር በኩል ክልሉ ያለውን ሚና እንዲያሳድግ ቅንጅታዊ አሰራር ይጠናከራል ብለዋል።

‎ለዚህም ተደራጅተው ፈቃድ ያገኙ ወርቅ አምራች ማኅበራት በመሉ አቅም ወደ ተግባር እንዲገቡ በማድረግና አዳዲስ ማኅበራትን በማሰማራት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስቀጠል እንደሚሰራ ተገልጿል።