May 13, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ የሚካሄድበት ስታዲየም እየሰመጠ ነው

የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት፣ የመክፈቻው ጨዋታ የሚካሄድበት ታሪካዊው የሜክሲኮ “ኢስታዲዮ አዝቴካ” (Estadio Azteca) የመስመጥ አደጋ እያጋጠመው መሆኑ ተሰማ።

ይህ ድንገተኛ ሁኔታ በስፖርት አፍቃሪዎች እና በውድድሩ አዘጋጆች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል።

የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ (NASA) የስታዲየሙን ሁኔታ ከጠፈር ሆኖ በራዳር በቅርበት እየተከታተለው የሚገኝ ሲሆን፣ ናሳ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ሜክሲኮ ሲቲ ያለችበት መሬት በየዓመቱ እስከ 10 ኢንች (25 ሴ.ሜ) የሚደርስ የመስመጥ አደጋ እያጋጠማት ሲሆን፣ ስታዲየሙም የዚሁ አደጋ ሰለባ ሆኗል።

የናሳ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ከሆነ፣ ከከተማዋ በታች ያለው የከርሰ ምድር ውኃ መመናመን መሬቱ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሰምጥ ምክንያት ሆኗል።

በቅርቡ በስታዲየሙ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ የታደሙ ደጋፊዎችም፣ በስታዲየሙ ወለል ላይ ስንጥቆች እና የኮንክሪት ስብርባሪዎች መታየታቸውን በስጋት ገልጸዋል።

ኢስታዲዮ አዝቴካ በታሪክ ደማቅ ስም ያለው ስታዲየም ሲሆን፣ በተለይም ዲያጎ ማራዶና በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በእንግሊዝ ላይ “የእግዚአብሔር እጅ” (Hand of God) ተብላ የምትታወቀውን ግብ ያስቆጠረበት ታሪካዊ መድረክ ነው።

አዝቴካ ስታዲየም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የሜክሲኮ እና የደቡብ አፍሪካ የመክፈቻ ጨዋታን ጨምሮ አምስት ግጥሚያዎችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳ ስጋቱ እየጨመረ ቢመጣም፣ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የዓለም ዋንጫው ዝግጅት እና የመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት በታቀደለት መሠረት እንደሚቀጥል ተገልጿል።