August 26, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ማጣሪያ ቅድመ ዝግጅቱን ዛሬ ይጀምራል

በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅት ጥሪ የተደረገላቸው 40 ተጫዋቾችን በመያዝ ዛሬ ናሽናል ካምፒንግ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አሳውቋል።

የብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ቤንጃሚን ዚመር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር 3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅና ከ22 ዓመታት በኋላ ለ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ያደረጉ ሲሆን በውድድሩም ቡድኑ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ለዓለም ዋንጫ ለማሳለፍ ከጫፍ አድርሰውት እንደነበር ይታወሳል።

በምክትል አሰልጣኝነት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታላላቅ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ፍፁም ገብረማርያም የተሾመ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈውና በጅማ አባ ቡና እንዲሁም በመቻል (ከ17 ዓመት በታች ቡድን) በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የሠራው ገመቹ በቀለ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት የሚሠራ ይሆናል።