የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዝቦች ክልል ከሚገኙ አቅራቢ ነጋዴዎች ጋር በወቅታዊ የቡና ገበያ ነባራዊ ሁኔታን አስመልክቶ በቦንጋ ከተማ ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክሩ ቡና ያከማቹ አምራቾች እና ነጋዴዎች በአፋጣኝ ለገበያ እነዲያወጡ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ በኢትዮጵያ ከ30 ሚሊየን በላይ ዜጎች የኑሮ መሠረት ከቡና ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።
በቡና የግብይት ስርዓት ውስጥ የደላላዎች ጣልቃ ገብነት በመኖሩ የአምራችና አቅራቢ ነጋደዎች የመረጃ ልውውጥ ክፍተት ለዘርፉ ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።
ቡና የሀገር ኢኮኖሚ ምንጭ እንደመሆኑ ከግብይት ስርዓት ውጪ ያከማቹ አካላት በአፋጣኝ በእጃቸው ያለውን ምርት ለገበያ ማቅረብ አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ ሰብስቤ ሻዎኖ በበኩላቸው ቡና የኤክስፖርት ምርት እንደመሆኑ የሽያጭ ዋጋ በዓለም ገበያ እንደሚወሰን ተናግረዋል።
ቡናን ከተፈቀደው ጊዜ በላይ በመጋዘን ማቆየት ለጥራት ጉድለት ከማጋለጡም ባለፈ በሚለዋወጠው የአለም ገበያ ምክንያት ላልተፈለገ ኪሳራ እንዳይዳረጉ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚተላለፉ የአሠራር መመሪያዎችንና መረጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ቡናን በወቅቱ አዘጋጅቶ ለማቅረብ በኢንዱስትሪዎች የነዳጅ እጥረት ኤክፖርተሮች ምርት ከተረከቡ በኋላ ሙሉ ክፍያ አለመፈጸም ችግሮች መኖራቸውን ተሳታፊዎች አንስተዋል።
ከደረሰኝ ህትመት ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር በአንድ ድርጅት ብቻ እንዲታተም መደረጉ ለከፍተኛ መጉላላት እየዳረገ በመሆኑ አማራጭ እድሎች እንዲመቻቹ ጠይቀዋል።
በሌላ መልኩ የጫኚና አውራጅ ሠራተኞች የጭነት ትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ምርትን በአፋጣኝ ገበያ ለማቅረብ ተግዳሮት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለዘርፉ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ሲል ቦንጋ ኤፍ ኤም ዘግቧል።
More Stories
ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ53 ከአፍሪካ ሀገራት የተመረተ የቡና ምርት ወደ ገበያዋ እንዲገቡ ክፍት አደረገች
ዓመታዊ የወጪ ንግድ ያስገኘው ገቢ ጨምሯል ተባለ
አዲሱ የማዕድንና ኢንዱስትሪ ትስስር