February 26, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

“በ250 ሚልዮን ዩሮ” ያማልን አልሸጥም ያለው ባርሴሎና

ማሻ፤ የካቲት 17/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8):- ለወጣቱ ስፔናዊው አነጋጋሪ ኮከብ ላሚን ያማል የፈረንሳዩ ሀያል ክለብ ፓሪሴንት ዤርሜይን አቅርቦት የነበረውን የአለም ክብረወሰን የሆነ 250 ሚልዮን ዩሮ የዝውውር ጥያቄ ውድቅ አድርገነዋል ሲሉ የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት ሁዋን ላፖርታ ተናግረዋል፡፡

በየጊዜው ከፍ እያለ በመጣው የተጨዋቾች የዝውውር ዋጋ አሁንም ክብረወሰን ሆኖ የዘለቀው ፓሪሴንት ዤርሜይን እኤአ በ2017 ብራዚላዊው ጥበበኛ ኔይማር ጁኒየርን ከባርሴሎና በ222 ሚልዮን ዩሮ ያስፈረመበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሀብታም የሆነው የፓሪሱ ክለብ ሌላ ክብረወሰን ለመስበር በማሰብ ታድያ ከአንድ አመት በፊት ወጣቱን የባርሴሎና ኮከብ ላሚን ያማልን ለማዛወር የ250 ሚልዮን ዩሮ የዝውውር ጥያቄ አቅርቦ ክለቡ ውድቅ ማድረጉን የባርሴሎናው ፕሬዝዳንት ሁዋን ላፖርታ ይፋ አድርገዋል፡፡

ላፖርታ እንደተናገሩት ያማል 17 አመቱ እያለ ፒኤስጂ ያቀረበልን የማይታመን ገንዘብ ነበር፤አንዳንዶች ይሄንን አለመቀበላችን እንደ እብድ አይተውናል፤ነገር ግን በፍጹም የማንነካው ኮከባችን በመሆኑ ምክንያት ለመቀበል ፍቃደኛ አልነበርንም ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወደፊት የአለም እግር ኳስን ይቆጣጠራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ከዋክብቶች መካከል አንዱ የሆነው የ18 አመቱ ኮከብ ላሚን ያማል የበርካቶችን ቀልብ መሳቡን የቀጠለ ሲሆን ከእድሜው በላይ ብስለት የተሞላበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎቹ ቀጣዩ የአለማችን ኮከብ ይሆናል ተብሎ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ከዋክብቶችን በማፍራት ከማይነጥፈው ላማሲያ አካዳሚ የተገኘው ትንሹ ኮከብ ከወዲሁ በበርካታ ሽልማቶች መታጀብ የቻለ ሲሆን በተጨማሪም እኤአ እስከ 2031 ድረስ በብሉግራናዎቹ ቤት የሚያቆየውን የ6 አመት የውል ስምምነት በመፈራረም ቀዳሚው የክለቡ ተከፋይ ተጨዋች ለመሆን እንደበቃ ይታወቃል፡፡

ያማል በለጋነት ላይ የሚገኝ ተጨዋች እንደመሆኑ ከሜዳ ውጭ እያሳየ በሚገኘው ድርጊቶች እንዲሁም በየጊዜው በሚደርስበት ከፍተኛ ጫናዎች ምክንያት ብዙዎች የወደፊት የእግር ኳስ ህይወቱ እንዳይበላሽ በሚል በስጋት መልክ የሚያነሱት ብቸኛ ጥያቄ ነው፡፡

ያማል በያዝነው የውድድር አመት በ33 ጨዋታዎች 15 ጎሎችን አስቆጥሮ 12 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡