February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው  የደካ ዳሩ ሰላም መስጊድ ተመረቀ

ማሻ፣ ጥር 03/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ካፋ ዞን ደካ ከተማ ውስጥ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ሙሉ ተሳትፎ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ግዙፉ የዳሩ ሰላም መስጊድ በደማቅ ስነ-ስርዓት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

በ1,950 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ ዘመናዊ መስጊድ፣ ለከተማው ተጨማሪ ውበትና ቅርስ ከመሆኑም ባሻገር፣ የማህበረሰቡን የመተባበርና የአንድነት መንፈስ በተግባር ያሳየ ፕሮጀክት መሆኑ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ ኢትዮጵያ ያላት የሃይማኖት መቻቻልና መከባበር ልምድ ልዩ የሚያደርጋት ሀብቷ ነው ሲሉ ገልጸዋል። መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች በእኩል ዓይን እንደሚመለከትና የሙስሊሙ ማህበረሰብ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ እንደሚያደንቅ ጠቁመው፣ ህዝበ ሙስሊሙ የበኩሉን ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፣ አስተዳደሩ በዞኑ ውስጥ ለሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት፣ የመስጊድ ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የደካ ከተማ ከንቲባ አቶ አድነው ኃይሌም መስጊዱ ለከተማው ውበት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ በግንባታው ሂደት ውስጥ አሻራቸውን ላሳረፉ ግለሰቦችና ተቋማት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፈትዋ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢና የምስራቅ አፍሪካ ኡለማዎች ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ደጄላን ከድር የመስጊዱን መመረቅ አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸዉን የደካ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ዘግቧል ።