ማሻ፤ ታህሳስ 22/2014 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፍትሕ ቢሮ ከሸካ ዞን ፍትሕ መምሪያ ጋር በመተባበር በሸካ ዞን ለሚገኙ አቃቤያነ ሕጎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
ሥልጠናው በአዲሱ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 እንዲሁም በወንጀል ስነ-ሥርዓትና በዐቃቢያነ ህግ የስነ-ምግባር ደንብ ዙሪያ ያተኮረ ነው።
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ታመነ ታደሰ እንደገለጹት፤ የአቃቤያነ ሕግን የሙያ ዕውቀትና የሥነ-ምግባር አፈጻጸም ማጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የሕዝብን አመኔታ ለማጎልበት ወሳኝ ተግባር ነው።
አቃቤያነ ሕግ የሕዝብን አመኔታ ማግኘት የሚችሉት በታማኝነትና በበቂ ዕውቀት ላይ ተመስርተው የሕዝብና የመንግሥትን አደራ ሲወጡ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አቶ ታመነ አክለውም፣ አዲሱ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲሰፍንና ተገማችነት ያለው የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ ሰልጣኞች በሥልጠናው የሚቀስሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ አሳስበዋል።
የሸካ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አድራሮ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው አቃቤያነ ሕግ ከአዳዲስ መመሪያዎች ጋር እንዲተዋወቁና በተግባር የሚያጋጥሟቸውን የሕግ አተገባበር ክፍተቶች እንዲሞሉ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመሆኑም ሠልጣኞች ሥልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ለሥራቸው ስኬታማነት እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ሥልጠና ላይ ከሸካ ዞን የተውጣጡ አቃቤያነ ሕግ እየተሳተፉ ሲሆን፣ ሥልጠናው በዞኑ ቀልጣፋና ፍትሐዊ የሕግ አገልግሎት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
#መ.ኮ.ጉ
More Stories
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፡- በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ወል ትርክትን የመገንባት ጉዞ
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ ስኬታማነት ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ተባለ
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ያደሩ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር አዳዲሶቹን ጀምሮ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።