ከ47 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤና መሪዎችና ሚኒስትሮች የሚመክሩበት 76ኛው የአፍሪካ ጤና ኮሚቴ (WHO RC76) ጉባኤ፣ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተገኙበት በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ደማቅ የክብር እውቅና እና ሽኝት ተደርጎላቸዋል። የአለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ጃናቢ፣ ጉባኤው ዶክተር ቴዎድሮስ በዋና ዳይሬክተርነት ቦታቸው ላይ እያሉ የሚካሄድ የመጨረሻው አህጉራዊ ስብሰባ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት ግንባታ ላበረከቱት ታሪካዊ አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ዓለም አቀፍ የጤና ተግዳሮቶችን እየታገሉ ለአፍሪካ የሰጡት ልዩ ትኩረት የማይዘነጋ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካውያን ለሕክምና ወደ ውጭ በመሄድ በየዓመቱ የሚያወጡትን 7 ቢሊዮን ዶላር ለመቀነስ፣ ታካሚዎችን ከአፍሪካውያን ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኝ የተቀናጀ የልዩ ሕክምና አገልግሎት ካርታ ይፋ መደረጉን ዶክተር መሐመድ ጃናቢ ገልጸዋል። “የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ለአፍሪካ ሊውል ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቀሱት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተሩ፣ እስካሁን የ5 ሺሕ 290 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ይፋ አድርገዋል።
ወረርሽኙን ለመግታት የጤና ባለሙያዎች ወደ ማህበረሰቡ በነፃነት እንዲገቡ የ60 ቀናት የሰዋዊ እርዳታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለተፋላሚ ወገኖች ጥሪ አቅርበዋል። “ሰላም እኛ ልንሰጠው የምንችለው ትልቁ መድኃኒት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አፍሪካ የራሷን የጤና ዕጣ ፈንታ ለመምራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
More Stories
ከ 315 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የምጠበቀው የTELCOM+ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ፊዴ ቀበሌ በይፋ ተጀመረ
በ8 ክልሎች ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የጤና ምርመራ ዘመቻ ተጀመረ
ዘመቻው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቅቋል፦ የክልሉ ጤና ቢሮ