የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ኢትዮጵያውያን በምክክሩ የተገኘውን ስኬት በማጠናከር በጋራ የወደፊት ራዕይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በ1958 የናይጄሪያን ጦር የተቀላቀሉና በናይጄሪያ ጦር ዋና አዛዥ እስከመሆን ያገለገሉ፣ ናይጄሪያን ለስምንት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩ፣ በአፍሪካ ህብረት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ እና በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው፡፡
ኦባሳንጆ አንድም የአፍሪካ ህብረት ተልዕኳቸውን ለመወጣት እልፍ ሲልም ካላቸው የካበተ የፖለቲካ ልምድ ለኢትዮጵያውያን አባታዊ ምክራቸውን ለመስጠት በምክክር ኮሚሽኑ ማጠቃለያ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም ኦባሳንጆ ብሔራዊ ምክክሩን በአፍሪካ ደረጃ ታሪካዊ ርምጃ ሲሉ አድንቀው ÷ ኢትዮጵያ የወደፊት እድሏን ለመወሰን እና ከግጭትና ከመከፋፈል ይልቅ በውይይትና በመግባባት እንድትጓዝ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡
እውነተኛ ሰላም የሚመጣው ከአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከሁሉም መሆኑን የገለፁት ኦባሳንጆ ÷ የምክክር ኮሚሽን ይህን በመረዳት በአጀንዳ አሰባሰብ ሒደት ውስጥ ሁሉንም ማሳተፍ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የምክክሩ ስኬት የሚለካው በአጀንዳዎች ላይ በተደረሱ ስምምነቶች ብቻ ሳይሆን ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር በሚኖረው ቁርጠኝ ነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ምክክሩ ወደ ተግባር ሲቀየር የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠባት እና የተረጋጋች ሀገር እንደምትሆን እምነታቸው መሆኑን ገልጸው ÷ ሰላም ከተረጋገጠ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ ይሆናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአንድ ምዕት ዓመት በኋላ በዓለም ላይ ካሉ የበለፀጉ ሀገራት መካከል አንዷ የምትሆንበት አቅም እንዳላት አብራርተዋል፡፡
ይህ እንዲሳካ ግን ኢትዮጵያውያን ያለፈውን የግጭት፣ የጦርነት፣ የጥቃት፣ የመከፋፈልና የውድመት ታሪክ በመተው በጋራ የወደፊት ራዕይ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ያላት ታሪክ፣ ብዝሃነት፣ የሰው ኃይልና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነቷ ለሀገሪቱ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰው ÷በሀገሪቱ የተደረገው ምክክር ሰላም፣ አንድነት፣ብልጽግናና የተሻለ የወደፊት እድል ይዞ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
የምክክሩ ውጤቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ እንዲሁም በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም እና እድገት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የአፍሪካ ህብረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)
More Stories
በምክክሩ ለሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በነጻነት ተወያይተናል – ተመካካሪዎች
ኢትዮጵያ የደን ሽፋንን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የምታከናውነውን ጥረት ኖርዌይ ትደግፋለች
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን ችግሮችን በጋራ መክረው እንዲፈቱ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል