July 22, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ከ 315 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ የምጠበቀው የTELCOM+ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ ፊዴ ቀበሌ በይፋ ተጀመረ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሸካ ዞን ከሐምሌ 13/2018 ዓ/ም ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት በሁሉም መዋቅሮች የምቆይ TELCOM+ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ እንደምሰጥ የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወየሳ እንደገለጹት፤ መንግስት በማህበራዊ ዘርፍ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥና የጤና ተደራሽነት ችግርን ለመቅረፍ ይህንን ነፃ የተቀናጀ የጤና ዘመቻ አስጀምሯል ብለዋል።

በዞኑ በሚገኙ 64 ቀበሌዎች በአምስት የአገልግሎት አይነቶች ከ315 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አብራርተዋል።

ለዘመቻው ስኬት እስከ ቀበሌ ድረስ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሲካሄድ መቆየቱን ያነሱት ኃላፊው፣ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

የሸካ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከድር ገምሳ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ለህዝብ ከገባው ቃል ውስጥ ማህበራዊ ልማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ አምራች ዜጋ ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘመቻው በሁሉም ቀበሌዎች በንቅናቄ እንደሚካሄድ በመግለጽም ፕሮግራሙን በይፋ አስጀምረዋል።

የየኪ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስማማው ጎጅቶ፣ መንግስት የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በመደበኛና በዘመቻ መልክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ነዋሪው በዘመቻው በነቂስ እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከል ባለሙያ አቶ አስማማው አለሙ እንደገለፁት ፤ ዘመቻው በሰለጠኑ ባለሙያዎች በአንድ ማዕከል የሚሰጥ ሲሆን በዘመቻውም የቲቢ በሽታ ልየታና ህክምና፣ የአይን በሽታ ልየታ፣ የወባ በሽታ ምርመራ፣ የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ እና የኦንኮሰርሲያሲስ (Onchocerciasis) መድኃኒት እደላ አገልግሎቶች እንደምሰጡ ተናግረዋል ።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ቀደም ሲል እነዚህን ህክምናዎች ለማግኘት ከፍተኛ ጊዜና ወጪ ይጠይቅባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በአቅራቢያቸው በአንድ ማዕከል በነፃ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።