August 18, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ዘላቂ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ፣ አካታች የፖለቲካ ባህል እና የሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ መደላድል

በኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ዘላቂ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት የመገንባት ሂደት ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አካቶ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

የፖለቲካ ባህልን ከግጭት፣ ከጥፋት እና ከዋልታ ረገጥ አካሄድ ወደ ትብብር፣ ውይይት እና አብሮነት ለመቀየር የሚደረጉ ስራዎች የዚሁ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዋና ማዕከል ናቸው።

የሀገራችንን የፖለቲካ ታሪክ ሲፈታተን የቆየውን በግጭት የመሸናነፍ አዙሪት በመስበር፣ የታሪካዊ ስብራቶችን በመጠገን እና የጋራ ሀገራዊ ራዕይን ለመሰነቅ አዲስ ተቋማዊ አቅጣጫ እየተቀየሰ ነው።

ለዚህ እውን መሆን ደግሞ አካታች የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች በሀገር ጉዳይ ላይ የሚመካከሩበት የጋራ መድረክ እንዲኖር ማድረግ እና በውሳኔ ሰጪነት ደረጃ የሴቶችንና የሁሉንም ክፍሎች ተሳትፎ ማሳደግ ፍትሃዊ ስርዓት ለመገንባት ትልቅ መንገድ ከፍቷል።

የሀገረ-መንግሥት ግንባታን ከሚያደናቅፉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የሆኑትን ወገንተኝነት የሚያንጸባርቁ ነጠላ ትርክቶች ለመተካት፣ የብዝሃነትን እና የህብረ-ብሔራዊነትን ውበት የሚያጎላ አሰባሳቢ የጋራ ትርክት መገንባት ወሳኝ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የውስጥ አንድነትን ማጽናት የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ፣ በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችን በውይይት ፈትቶ ጠንካራ የውስጥ አንድነት መፍጠር የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከማስቀረቱም በላይ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደራዳሪነት ከፍ ያደርገዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሀገራዊ ምክክሩ በኃይል የመፍታት ጎጂ ልማድን በማስቀረት፣ በሀገር በቀል የእርቅ እና የይቅርታ እሴቶች ላይ ተመስርቶ ታሪካዊ ቅሬታዎችን እና መዋቅራዊ ስብራቶችን ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመጠገን የሚያስችል ጽኑ መደላድል እየጣለ ይገኛል።

ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት የሚመሰረተው በጠንካራ ተቋማት እና በጠራ እሳቤ በሚመራ አመራር ላይ በመሆኑ፣ የመደመር ፍልስፍና ሀገራዊ አቅሞችን በመሰናሰል፣ ያለፉ መልካም እሴቶችን በማስቀጠል እና ስህተቶችን በማረም ሀገርን በጋራ ጥረት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እሳቤ ሆኖ ያገለግላል።

ይሄው ተቋማዊ ብቃት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስራዎችን በስኬት ለማከናወን የሚያስችል የሀገረ-መንግሥቱን ኢኮኖሚያዊ መሰረት ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ፣ የተጀመሩትን የምክክርና የግንባታ ሂደቶች በጋራ ርብርብ አጠናክሮ ማስቀጠል ለነገው ትውልድ የምትመች እና የጸናች ሀገር ለማስተላለፍ ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ ነው።

#EBC