August 16, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮምሽን አስታውቋል፡፡

በክልሉ በአዲሱ በጀት አመት በደረሰው 28 የትራፊክ አደጋዎች ለ51 ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል።

በትራንስፖርት ዘርፍ በተለይም ከተተመነው ታሪፍ በላይ ጭማሪ የሚያስከፍሉ እና ትርፍ ሰው መጫን አንዱ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆነ መጥቷል።

በተለይም ከታርፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ እንዲሁም ናፍጣ ከቀዱ በኋላ ወደስምሪት የማይገቡ አሽከርካሪዎች በመኖራቸውን ይህንን ለማረም እና አስፈላጊውን የቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋትም የምልከታ ስራዎች በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ በሚገኙ መነኻሪያዎች ላይ ማድረጋቸውን ነው የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር አደጋ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮምሽነር መኮንን መንገሻ የተናገሩት።

በዚህም በመናኻሪያው የተሳፋሪ ፍሰት መኖሩን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ማስተካከል ከመቻላቸውም በላይ ከታርፍ በላይ በሚያስከፍሉት እና ትርፍ በሚጭኑት ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

በክልሉ ከባለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ 28 የትራፊክ አደጋዎች መድረሱን የተናገሩት ምክትል ኮምሽነሩ በዚህም 51 ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤውም በምሽት ማሽከርከር እና የባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ከተከሰቱት አደጋዎች ውስጥም 15 አደጋዎች በቤንች ሸኮ ዞን የተከሰቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በህግ ማስከበሩ ዙሪያ ላይ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን መቆም እንዳለበት ተናገረው በተለይም በፍሰት ተቆጣጣሪ አባላቶቹ ላይ የሚታየውን የስነምግባር ችግሮችም ካሉም ተገቢ ጥቆማ ህብረተሰቡ ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከል ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ታከለ በበኩላቸው ከትራንስፖርት ታሪፍ እና ትርፍ ሰው መጫን ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታ መኖራቸውን ጠቁመው ህገወጥ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መጥቷልም ብለዋል።

በህብረተሰቡ በኩልም ከተቆጣጣሪ አካል ጎን ከመሆን ይልቅም ለህገወጡ መወገን ችግሮች የሚታይ በመሆኑ ህዝቡ መረጃ በመስጠት በኩልም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል ።

በዞኑ በአንድ ወር ውስጥ አስራ አምስት የትራፊክ አደጋዎች መድረሳቸውን ጠቁመው በተለይም የአደጋ መንስኤ የሆኑት የባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ተገቢ የሆነ የቁጥጥር ስራ ይሰራልም ብለዋል ።

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪ ዋና ሳጂን ፍቅሩ ተስፋዬ በበኩላቸው በተለይም በከተማው የትራፊክ አደጋ በባለሁለት የሞተር ሳይክል ሞተሮች እንደሚፈጸምና ይህንንም ለማረም የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል ።

ከትራንስፖርት እጥረቱ ጋር አርተፍሻል እጥረት መኖሩን ጠቁመው በተለይም ለህዝብ ተሽከርካሪዎች ናፍጣ ቅድሚያ እንድቀዱ ቢደረግም አንዳንድ አሽከርካሪዎች ናፍጣ ከቀዱ በኋላ ወደስምሪት በማይገቡ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል በዚሁም በስድስት ተሽከርካሪዎች ላይ የአንድ ወር ቅጣት መጣሉንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም ተገቢ መረጃ ለፍሰት ተቆጣጣሪ በመስጠት በኩል አጋር በመሆን መብቱን በተገቢው ሊያስከብር ይገባልም ብለዋል።

ተሳፋሪዎች በበኩላቸውም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍ፣ ትርፍ በሚጭኑ፣ በተገቢው ስምሪት በማይሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል። መረጃዉ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ነዉ።