August 10, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላም መሰረት የሚጥል ነው

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚጥል ነው አሉ የዳያስፖራ ማህበረሰብና የሲቪል ማህበረሰብ ተመካካሪዎች፡፡

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የዳያስፓራ ማህበረሰብ ወኪል ተመካካሪ አቶ ልዑልሰገድ አበበ በምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶች በንግግርና በመደማመጥ ወደ የጋራ መግባባት እየተቃረቡ ነው ብለዋል።

ከጉባኤው የሚፈልቀው የጋራ ሀሳብም በአንዳንድ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ የሆኑ ልዩነቶችን በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ ሰላምን ማስረከብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ሌላው ተመካካሪ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ወኪል ተመካካሪ አቶ ጌትነት ለማ፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከትንንሽ የውይይት ቡድኖች ጀምሮ በከፍተኛ መደማመጥና በአካታች አሠራር እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ እንደዚህ ዓይነት ዕድል አግኝተው እንደማያውቁ ጠቁመው፤ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ህብረት እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወኪል ተመካካሪ ደሳለኝ ክፍሉ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉባኤው ሀሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበትና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የጋራ መግባባት የሚያሻግር መሆኑን ገልጸዋል።

ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊ፣ የተረጋጋችና የተባበረች ሀገር ማስረከብ የሚያስችሉ የጋራ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መድረክ መሆኑንም አስረድተዋል።

መነጋገራችን፣ መመካከራችንና መደማመጣችን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የመግባባት ምዕራፍ ያሻግራታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡