August 13, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

ማንቼስተር ዩናይትድ የ18 ዓመቱን ክርስቲያኖ ሮናልዶን ያስፈረመበት ታሪካዊ አጋጣሚ

እ.ኤ.አ. በ2003 በዚች ዕለት (ነሐሴ 6 ቀን 1995 ዓ.ም) ማንቼስተር ዩናይትድ የወደፊቱን የዓለም እግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ከስፖርቲንግ ሊዝበን በ12.24 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ በይፋ ያስፈረመበት ታሪካዊ ቀን ነበር።

የ18 ዓመቱ ወጣት ሮናልዶ በኦልድ ትራፎርድ የነበረው ቆይታ በቀጣዮቹ ዓመታት የእግር ኳስ ታሪክን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ይሆናል ብሎ የገመተ ጥቂት ነበር።

በሰር አሌክስ ፈርጉሰን የሚመሩት ዩናይትዶች ተጫዋቹን ለማስፈረም የወሰኑት፣ ከዝውውሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ስፖርቲንግ ሊዝበን ዩናይትድን 3 ለ 1 ባሸነፈበት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ በሳየው ድንቅ ብቃት የማንቼስተር ተጫዋቾች በራሳቸው አሰልጣኙን ተጫዋቹን እንዲያስፈርሙት ካሳሰቡ በኋላ ነበር።

በኦልድ ትራፎርድ ቆይታው ሮናልዶ ከወጣት አክስቴንሲ ወደ ፍጹም የግብ ማሽንነት የተቀየረ ሲሆን፣ ለክለቡ ባደረጋቸው 292 ጨዋታዎች 118 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

ከቀይ ሰይጣኖቹ ጋር 3 የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን፣ 1 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፣ 1 የኤፍ ኤ ካፕ እና 2 የሊግ ካፕ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።

በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2008 በዩናይትድ ማሊያ የመጀመሪያውን የባሎንዶር ሽልማት ክብር የተቀዳጀ ሲሆን፣ ከጆርጅ ቤስት በኋላ ይህንን ሽልማት ያሸነፈ የመጀመሪያው የዩናይትድ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

ከስድስት የስኬት ዓመታት በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በ2009 በወቅቱ የዓለማችን ውድ የዝውውር ዋጋ በሆነው 80 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ሪያል ማድሪድ በማምራት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፈተ።

የነሐሴ 6ቱ ዝውውር ለማንቼስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን ለዓለም እግር ኳስ ትልቅ ታሪክ የተጻፈበት ዕለት ሆኖ ይዘከራል።