August 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መረሃ ግብርን ባህል በማድረግ በሕዝቦች ዘንድ መተሳሰብን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ።

እንደሀገር ”በጎነት ለኢትዮጽያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በኢፌዴሪ ስራና ክህሎት ሚንስቴር ድጋፍ የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ሥራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በወቅቱ እንደተናገሩት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በ14 ትኩረት ዘርፎች በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት በክልሉ መከናወናቸውን ጠቁመው ህብረተሰቡ ደህንነቱ እንዲጠበቅ በችግኝ ተከላና ሌሎች የበጎ ፍቃድ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድቷል ።

በክልሉም ወደ 2ሚልዮን የሚጠጉ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይህ መረሃ ግብር ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር የጋራ ትርክትን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል ።

በቀጣይ በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች ደረጃውን የጠበቀ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እንደሚከናወን ጠቁመዋል ።

ከኢፌዴሪ ስራ ክሎት ሚንስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ ቤንች ሸኮዞንና ሸካ ዞን የበጎ አድራጎት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢፌዴሪ ስራና ክሎት ምኒስቴር ደኤታ ተሻለ በረኤቻ (ዶ/ር) ባለፉት አመታት የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን ገልፀዋል ።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ የመጣና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር ስራ በተለያዩ ክልሎች ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው በክልሉ ቤንች ሸኮና ሸካ ዞኖች ሚኒስቴር መስራቤቱ የበጎ አድራጎት ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

በዘንድሮ መረሃ ግብር በሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ፣የችግኝ ተከላና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀዋል ።

የክልሉ ስራና ክሎት ቢሮ ኃላፊ አብይ አንደሞ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበጎ አድራጎት ተግባር በመደመር ዕሳቤ ከመንግስት መደበኛ ስራ ጎን ለጎን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር ድንበር የለሽ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።

በዚህም የተቋማት ሰራተኞች በተግባሩ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልፀው ወደ 20ሺ የሚጠጉ ችግኞችን በተለያዩ አካባቢዎች በመትከል አሻራቸውን እያስቀመጡ መሆኑንም ገልፀዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ስራና ክሎት ሚንስቴር ሚኒስትር ደኤታ ተሻለ በረኤቻ (ዶ/ር)፣ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንና ሌሎችም የክልል፣ የዞንና የከተማ ስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።