በበጀት ዓመቱ የንግዱን ዘርፍ በማዘመንና በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማገዝ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ”የተደራጀ የዲጂታል አገልግሎት ለዘመናዊ የንግድ አገልግሎት” በሚል መሪ ሀሳብ የሴክተር ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ የንግድ ዘርፉን ከማዘመን በተጨማሪ ዲጂታል አገልግሎትን በማጠናከር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይ የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የንግድ ፈቃድና መሠል አገልግሎቶችን በኦን ላይን በመፈጸም የንግዱን ማህበረሰብ የአገልግሎት እርካታ 96 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
የንግድ ፈቃድና የገበያ ቁጥጥርን በማጠናከር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ 805 ተጨማሪ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች መከፈታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በእዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለማህበረሰቡ በቀጥታ ማቅረብ በመቻሉ ገበያው እየተረጋጋ መምጣቱን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም አውስተዋል።
መንግስት የተከተለው የፖሊሲ አማራጭ ለዘርፉ ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ጠቁመው፤ በተለይ የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ አቅጣጫ የኢኮኖሚ መሰረትን በማስፋት ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የቁም እንስሳት ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ትኩረት እንደተሰጠና፣ ለእዚህም ከ10 በላይ የቁም እንስሳት የሽያጭ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥና እድገት የኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ የመደራደር አቅም እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰው፤ የተመዘገበውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ዘመኑን የዋጀና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በሴክተር ጉባኤው የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሁሉም ክልሎች የዘርፉ የቢሮ ሀላፊዎች እና ባለድርሻዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ የንግዱን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማገዝ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል – ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
More Stories
ኢትዮጵያ ለኬንያ 1 ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በ24 ብር ከ07 ሳንቲም ለማቅረብ ተስማማች
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ከሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሚዛን አማን ከተማ የቅድመ ምረቃ በረራ ጀምሯል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከክልሉ 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቧል