April 28, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የለንደን ማራቶን በታሪክ ግዙፉ የማራቶን ውድድር በመሆን የጊነስ ወርልድ ሪከርድ ተቀዳጀ

የ2026ቱ የቲሲኤስ (TCS) ለንደን ማራቶን፣ በታሪክ ከፍተኛ ተሳታፊዎች የተመዘገቡበት ውድድር በመሆን የጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ባለቤትነቱን በድጋሚ ተቀዳጅቷል።

በለንደን ጎዳናዎች ላይ በፈሰሱ 59 ሺህ 830 ሯጮች የታጀበው ይህ ውድድር፤ ቀደም ሲል የኒውዮርክ ማራቶን ይዞት የነበረውን የ59 ሺህ 226 ተሳታፊዎች ቁጥር በመብለጥ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

ይህ ውድድር ከቁጥር ባለፈ በአትሌቲክስ ጥበብም ዓለምን አስደምሟል። ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳዌ በ1፡59፡30 በመግባት የኤልዩድ ኪፕቾጌን ክብረ ወሰን ሲሰብር፣ ኢትዮጵያዊው የርቀት ንጉሥ ዮሚፍ ቀጀልቻ ጋር በመሆን ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች የገቡ የመጀመሪያዎቹ አትሌቶች በመሆን ስማቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈዋል።

በሴቶች ዘርፍም ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት አትሌቶች በአንድ ውድድር ከ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ በታች በመግባት አስገራሚ ብቃት አሳይተዋል።

ውድድሩ የፕሮፌሽናል አትሌቶች ብቻ ሳይሆን የልዩ ልዩ ትርኢቶችም መድረክ ነበር። ከቢግ ቤን ሰዓት እስከ ካርቱን ገጸ-ባህሪያት በለበሱ ሯጮች የታጀበው የለንደን ጎዳና፣ 38 አዳዲስ የክብረ ወሰን ዘርፎች እንዲመዘገቡ ምክንያት ሆኗል።

የለንደን ማራቶን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሂው ብራሸር ውድድሩ “አዲስ ታሪክ የተፃፈበት” መሆኑን ሲገልጹ፣ የጊነስ ወርልድ ሪከርድስ ዳይሬክተር ማርክ ማክኪንሌይ ደግሞ የለንደን እድገት “አስደናቂ” መሆኑን መስክረዋል።