March 16, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለዛምቤዚ ተፋሰስ አገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው



‎ማሻ፤ መጋቢት 8/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማስተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለዛምቤዚ ተፋሰስ አገራት ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡

‎ለዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ማጋሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው።

‎የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ዙሪያ የምታወራውን በተግባር የምትፈጽም አገር መሆኗን አስመስክራለች።

‎ባለፉት ዓመታት የተተከሉ 48 ቢሊዮን ችግኞች ስኬት ምንጩ የአመራሩና የሕዝቡ ቁርጠኝነት መሆኑን ጠቅሰው መርሃ-ግብሩ ለቀጣዩ ትውልድ ብልጽግና ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

‎የኮሚሽኑ አባላት በኢትዮጵያ ቆይታቸው እነዚህን ተጨባጭ ልምዶች ወደ አገራቸው ይዘው እንደሚሄዱና ኢትዮጵያም ከሌሎች አገራት ልምድ ለመጋራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

‎የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ፌሊክስ ሞሲ ንጋምላጎሲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ላይ የተመሠረቱ መፍትሔዎችን በመተግበር ረገድ ያላትን አህጉራዊ መሪነት በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል።

‎በተለይም ህዝብን በማስተባበር ረገድ የታየው ስኬት ለዛምቤዚ ተፋሰስ አገራት ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

‎ዋና ጸሐፊው አያይዘውም ኢትዮጵያ በግዙፍ መሠረተ ልማቶች ያስመዘገበችውን ስኬት አድንቀዋል፡፡

‎ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ግቤ 3 እና ኮይሻ ባሉ ፕሮጀክቶች የኃይል ዋስትናንና የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ለአፍሪካ በተግባር አሳይታለች ብለዋል፡፡

‎በዛምቤዚ ተፋሰስ ውስጥ እንደ ካሪባ እና ካቦራ ባሳ ያሉ ግድቦች ቢኖሩም፣ አሁንም ጥቅም ላይ ያልዋለ ሰፊ የውኃ ሀብት መኖሩን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፤ የኢትዮጵያ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ተሞክሮዎች ለተፋሰሱ አገራት ትልቅ መነሳሻ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

‎ኢዜአ