ማሻ፤ የካቲት 24/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) 130ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች የልዑካን ቡድን መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ቀደም ሲል በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ የትብብር ስምምነቶች ያሉበት የአፈፃፀም ደረጃ በጥልቀት የተገመገመ ሲሆን፣ በቀጣይም ትብብሩን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ አዳዲስ የመግባቢያ ሰነዶችን ጨምሮ በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ላይ በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
የዓድዋ ድል ከታሪካዊ ፋይዳው ባሻገር ዛሬ አፍሪካ ከፊቷ የተደቀኑባትን ወቅታዊ የፀጥታ እና የደኅንነት ስጋቶች በጋራ ለመመከት እንደ ትልቅ የመንፈስ ምንጭ እና የትብብር ማዕቀፍ ሊያገለግል እንደሚገባ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአህጉሪቱን ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ በመያዝ፣ በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በተለይም በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥልጠና እና በልምድ ልውውጥ መስኮች በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሽብርተኝነትን እና ድንበር ተሻጋሪ የፀጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ስልታዊ የትብብር አቅጣጫዎችም መቀመጣቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በውይይቱ የተሳተፉት የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ሰላም እና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ቀዳሚ እና የማይተካ ሚና አድንቀዋል።
የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል በዓልን በኢትዮጵያ ተገኝተው ከወንድሞቻቸው ጋር በጋራ በማክበራቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልጸው፣ በቀጣይም በጋራ የመከላከል አቅም ግንባታ ላይ በቁርጠኝነት ለመሥራት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት አረጋግጠዋል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ከማሳደጉም ባለፈ፣ የአህጉሪቱን የጋራ ደኅንነት እና ትሥሥር ለማረጋገጥ የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተዘግቧል።
More Stories
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቴፒ ግቢ አዘጋጅነት የተካሄደው14ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ተጠናቀቀ ።
ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ 21ሺ 5መቶ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቴፒ ምርት ጥራት ምርምርና ሰርትፍኬሽን ማዕከል አስታወቀ።
አሜሪካ ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት 25 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አጣች