ማሻ፣ ጥር 01/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍኤም 103.8) በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮችና ዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ስኬታማ እንዲሆንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱን ዘመናዊና ምቹ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁሞ ይህም መራጮችና ዕጩዎች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መጉላላትና ተፅዕኖ ለማስቀረት፣ አካል ጉዳተኞች (ዓይነ-ሥውራን) ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመዘግቡ ለማስቻል እንዲሁም መራጮች ቋሚ መለያ ቁጥር እንዲኖራቸውና የመረጃ አያያዝን ሥርዓት ለማስያዝ ያለመ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
በዚህም መራጮች “ምርጫዬ” የተባለውን የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም ራስን በራስ የመመዝገብ አማራጭ ተመቻችቶላቸዋል ብሏል።
በተጨማሪም በምርጫ ጣቢያዎች ታብሌቶችን በመጠቀም በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት የሚከናወን የምዝገባ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን፤ የቀደመውን አሠራር በመከተል በአካል በመገኘት በእጅ (በማንዋል) የመመዝገብ አማራጭም መጠቀም እንደሚቻል ተመልክቷል።
የምዝገባ ጊዜን በተመለከተ ቦርዱ ቀደም ሲል የራስን በራስ ምዝገባ ከጥር 15 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. ለማከናወን አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ሁሉም የምዝገባ አማራጮች ከፍትሐዊነት አንጻር በተመሳሳይ ጊዜ መጀመር ስላለባቸው ምዝገባው ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. እንዲከናወን ቦርዱ ተወስኗል።
በመሆኑም ቦርዱ የምዝገባ ምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር በሕጉ መሠረት ከምዝገባው ቀን አስቀድሞ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል
More Stories
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቴፒ ግቢ አዘጋጅነት የተካሄደው14ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ተጠናቀቀ ።
ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ 21ሺ 5መቶ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቴፒ ምርት ጥራት ምርምርና ሰርትፍኬሽን ማዕከል አስታወቀ።
አሜሪካ ከኢራን ጋር ባደረገችው ጦርነት 25 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አጣች