February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ ከመንግሥት ጎን  ድጋፋችንን እንቀጥላለን:-ተሳታፊዎች

ማሻ፣ ታህሳስ 17/2018 (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን አውራዳ ከተማ አስተዳደር ”የጉባ ብስራቶች፣የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ የዉይይት መድረክ ተካሂዷል።

የህዝባዊ ውይይት መድረክ ተሳታፊ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች፤ የመደመር መንግስት ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆነው ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እያደረገ ላለው ጉዞ እውቅና ሰጥቷል።

መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከማጠናቀቅ ባሻገር የጉባ ብስራት የሆኑ የነዳጅ፣ አፈር ማዳበሪያ  እንዲሁም ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በማስጀመሩ በማኅበረሰቡ አመስግነዋል።

መደመር መንግስት የጀመረውን ህዝባዊ መድረኮችን በማጠናከር የማኅበረሰቡን ችግር እያዳመጠ ተግባራትን በአንድነት መንፈስ ማሰብ፣ ማቀድና መፈጸም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ ከመንግሥት ጎን ቆመው እንደሚደግፉ ዝግጁነታቸውን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፤  ከቦንጋ-ጮጭ የአስፓልት መንገድ፣ሆስፒታል፣ ለከተማ ውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራ መንግስት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የነዳጅ እጥረት፣ የመንገድ መብራት፣ ያላለቀ የአውራዳ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታና ማስፋፊያ ሥራ ብሎም የቡና መገኛ ማኪራ ሀገራዊ አሻራ ያለው ፕሮጀክት እንዲሰራ አመልክተዋል ።

በውይይቱ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ እንደተናገሩት፤ በህዝባዊ ውይይት መድረኩ በመደመር መንግስትና ብልጽግና ፓርቲ እሳቤ መሠረት ተደርገው የሚነሱ  አስተያየቶች ለቀጣይ ጉዞ ስንቅ የሚሆኑ ናቸው።

በመድረኩም ማኅበረሰቡ ለፓርቲው ያለው አመኔታ በተግባር የተረጋገጠበት ነው ያሉት አቶ የሺዋስ፤  በህዝባዊ ውይይት መድረኩ ከሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ቅቡልነትና ዋጋ ያላቸው መመለስ የሚገባቸው ናቸው ያሉት።

ከማኅበረሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት መንግስት አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ህዝቡን በማስተባበር እንደሚሰራም ገልጸዉ  የከተሞችን የገቢ አቅም በማሳደግ የከተሞችን ውበት ለመጨመርና ተረጂነትን ለማስወገድ መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የቀይ ባህር በር ጥያቄ ህጋዊ፣ ቅብልነት ያለው፣ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ በመሆኑ ሀገራዊ ፣አፍሪካ እንዲሁም አለም አቀፍ ተሰሚነት እያገኘ በመሆኑ ምላሽ እስኪገኝ መንግስት በትኩረት የሚሰራ በመሆኑ ህዝቡ ትብብሩን እንዲያጠናክርም  ጠይቀዋል።

ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የካፋ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ታከለ ታምሩ ናቸው።

የመደመር መንግስት እሳቤ በመከተል የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ከንግግር ባለፈ በቁርጠኝነት ደክሞ በመስራት ውጤታማ ማድረግ ይገባናል ብለዋል አቶ ታከለ ታምሩ።

የአውራዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታረቀኝ ኃይሌ  በበኩላቸው የመደመር መንግስት አስተሳሰብ በመተግበር በከተማችን በሁሉም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች እንዲቀጥሉ ይሰራል ብለዋል ።

ከተማዋን ምቹና ማራኪ በማድረግ ለትውልድ የተስማማ እንድትሆን በከተማው አቅም መሰራት ያለበት ስራዎች ማህበረሰብ በማስተባበርና በማሳተፍ ይሰራል ነው ያሉት ከንቲባው። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ/ጉ ነው።