February 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ እየተከናወኑ የሚገኙ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች በክልልና በዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ምልከታ ተደረገ

ማሻ፣ ታህሳስ 17/2018 (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና የሸካ ዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት በአንድራቻ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።

​ቋሚ ኮሚቴው በወረዳው ባደረገው ቆይታ በዮኪጪጪ ቀበሌ የሚገኙትን የሞዴል አርሶአደር አቶ አዲሱ ሀይፎ የቡና ልማት እና የአሳ እርባታ ስራዎችን ተመልክቷል።

በተለይም የዓሳ ክላስተር ልማትን ይበልጥ ማሳደግና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት ለምግብ ዋስትናና ለተጨማሪ ገቢ ያለውን ፋይዳ ጉልህ መሆኑ ተጠቁሟል።

አርሶአደሩ የጀመሩት የተቀናጀ የግብርና ስራ በክላስተር ተደራጅቶ እንዲሰፋና የልምድ ልውውጥ መድረክ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል።

አርሶ አደሩ የግብርና ስራን በዘመናዊ መንገድ በማቀናጀት እያከናወኑት ያለው ተግባር ለአካባቢው አርሶ አደሮች ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑ ተገልጿል።

በተመሳሳይ በሽፋ ቀበሌ በተደራጁ ወጣቶች እየተከናወኑ ያሉ የቡና ልማት ስራዎች እና በገማድሮ ቀበሌ የገማድሮ ጤና ኬላ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት በቋሚ ኮሚቴው ተጎብኝቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በጤና ኬላው እየተሰጠ ባለው ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ዙሪያ ከፍተኛ አድናቆትና ጥሩ አስተያየት የሰጠ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ተቋማት ለማህበረሰቡ ቅርብ መሆናቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

​በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው በወረዳው የሚገኘውን የጌጫ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመጎብኘት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንቅስቃሴን ፣ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን እና ሌሎች የመማር ማስተማር ስራዎችን ተመልክቷል።

ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢያቸውን በማሳደግ ራሳቸውን እንዲችሉና የመማር ማስተማር ሂደቱ ፅዱና ምቹ በሆነ አካባቢ እንዲከናወን ትኩረት እንዲሰጥ፤

የተማሪዎችን መጠነ መቋረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የምገባ ፕሮግራሙ ውጤታማነት እንዲረጋገጥና አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤

​የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ እና ለልማት ስራዎች ስኬታማነት የህብረተሰቡ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ እንዲያድግ ጠይቀዋል።

​በግብርና ፣ በትምህርት እና በጤናው  ዘርፍ የተቀመጡ አቅጣጫዎች በተቀናጀ መልኩ ወደ ተግባር እንዲቀየሩ እና በየደረጃው ያለው የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት የግብርና እና ገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዲስምዕራፍ አለሙ  የታዩ ጥንካሬዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ክፍተቶች እንዲታረሙ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በዚህ የመስክ ምልከታ ላይ የክልሉ ምክር ቤት የግብርና እና ገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዲስምዕራፍ አለሙ፣ የሸካ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሰላማዊት ማሞ፣ የክልልና የዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል። ዘገባው የዞኑ መ/ኮ/ጉ ጸ/ቤት ነው