ማሻ፣ ታህሳስ 15/2018 (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በኮሚሽኑ አዘጋጅነት ለተከታታይ ሦስት ቀናት ትውልድን በስነ – ምግባር ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ቃል አዲስ ለተመደቡና እና ለነባር የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተሮች ፣ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል ።
ስልጠናው በየተቋማቱ የሚስተዋሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን አስቀድሞ ለመከላከል ብቃት ያላቸውን ባለሞያዎች ማፍራትን ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል ።
በወቅቱ ሙስና ዜጎች በፍትሃዊነት አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ከማድረግ ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በጋራ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል ፡፡
በዚህ ስልጠና ላይ የተሳተፉ አሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሙስናና ብልሹ አሰራር በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግኑኝነት በማሻከር በሀገር ኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን እያስከተለ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ሲሉ ገልፀዋል ።
ሙስናን መከላከል የሚቻለው ተቀናጅቶ በመስራት ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በስራቸው ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ።
የክልሉ ስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ በበኩላቸው በየተቋማቱ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በማሳጣት በመንግሥትና ህዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ሙስና እና ብልሹ አሰራር በመሆኑ በጋራ ትግል ማድረግ ያሰፈልጋል ብለዋል።
የኮሚሽኑን አዋጆችና አሰራር ስርዓቶችን ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር በማስተሳሰር ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የመዋጋት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ደግሞ የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አይበራ ናቸዉ ።
ስልጠናው የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጆችና መመሪያ መሠረት በማድረግ ሙስናና የጥቅም ግጭት ፣ሙስናን መከላከል ፣ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ማካሄድ እንዲሁም የአሰራር ሥርዓት ጥናትን ጨምሮ በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል ።
More Stories
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፡- በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ወል ትርክትን የመገንባት ጉዞ
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ ስኬታማነት ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ተባለ
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ያደሩ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር አዳዲሶቹን ጀምሮ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።