በ4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው ዘመናዊ የቡና እርሻ የክልሉን ገጽታ ይቀይራል ተብሏል፤ መንግስትም ሙሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጿል ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የሀገሪቱ የቡና ልማት ስራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ። “ቴፒ ግሪን ኮፊ ስቴት” የተሰኘው ድርጅት በክልሉ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ 1,500 ሄክታር መሬት ላይ በ4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የቡና እርሻ ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ በዚህ ዓመትም በ400 ሄክታር ላይ በመስኖ የሚለማ ዘመናዊ የቡና እርሻ ለመጀመር ዕንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ይፋ የሆነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የድርጅቱ ባለቤት የሆኑትን ኢንጂነር ታደሰ አድማሱን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
የቴፒ ግሪን ኮፊ ስቴት ባለቤት ኢንጂነር ታደሰ አድማሱ እንዳብራሩት፣ ፕሮጀክቱ ከተለመደው የቡና አዝመራ ስርዓት ፈጽሞ የተለየ ነው። ዘመናዊ የጠብታ መስኖ እና ተያያዥ የስማርት ግብርና ቴክኖሎጂ፣ ምርትን በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያስችሉ ሜካናይዝድ የማምረቻና ምርት መሰብሰቢያ ማሽነሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ነው።
“ግባችን ቡናን በብዛትና በጥራት አምርቶ፣ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ ማቅረብ ነው” ያሉት ኢንጂነር ታደሰ፣ የፕሮጀክቱ ስኬት የክልሉ መንግስትና ህዝብ ባለቤትነትና ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። በተለይም የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የጸጥታ ከለላ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ክትትል እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግስት የቡናን ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ የያዘውን ሀገራዊ ራዕይ “ቴፒ ግሪን ኮፊ ስቴት” በፍጥነት ተቀብሎ ወደ ተግባር በመግባቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
“ይህ ፕሮጀክት ለክልላችን የቡና ልማት ትልቅ እርምጃ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ፕሮጀክቱ ጥራት ያለዉ ቡና እንዲመረት፣ ለክልሉ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው እንዲሁም የአካባቢዉን ገቢ በእጅጉ እንደሚያሳድግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አክለውም “የክልሉ መንግስት በቡና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ፕሮጀክቱ የክልሉን የቡና ምርት በጣዕምና በጥራት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው፣ ለፕሮጀክቱ ስኬት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ የ4.5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ቡና በዓለም መድረክ ላይ በላቀ ጥራትና መጠን ለማቅረብ እንደሚያስችል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።
More Stories
ፕሬዚዳንት ታዬ ለፈረንጆች የገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ሀብትን በተገቢው ማሳወቅና ማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል ግልፀኝነት እንዲፈጠር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለፀ ።
ጃፓን የዓለማችን ትልቁን የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዳግም ስራ ልታስጀምር ነው