ጋዜጣ_ፕላስ | የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋናው ጉባዔ በጥር ወር መጨረሻ 2018 ዓ.ም እንደሚከናወንና በትግራይ ክልል የሚከናወኑ የምክክር ሥራዎችም በያዝነው ሳምንት እንደሚጀመሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ለኮሚሽኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰጠው የሥራ ጊዜ እስከ የካቲት አጋማሽ 2018 ዓ.ም ድረስ በመሆኑ፣ ዋናው ጉባዔ የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት በጥር ወር መጨረሻ እንዲካሄድ ታቅዷል።
በዚሁ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ከ4 ሺህ በላይ ተወካዮች እንደሚሳተፉ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ለጉባዔው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከመደረጉ በፊት በትግራይ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሥራው የሚሳተፉ ሰዎችን የመመልመልና የማሰልጠን ተግባራት በያዝነው ሳምንት የሚጀመሩ ሲሆን፤ የቀረው ጊዜ አጭር በመሆኑ በትግራይ ክልል የሚከናወነው የምክክር ሥራ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች አጀንዳዎችን የማሰባሰብና ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል የምክክር ሂደት መጀመርም መላ ሀገሪቱን ያካተተ የምክክር መድረክ ለመፍጠር ለተያዘው ግብ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተመላክቷል።
More Stories
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፡- በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ወል ትርክትን የመገንባት ጉዞ
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ ስኬታማነት ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ተባለ
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግስት ያደሩ በርካታ የልማት ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር አዳዲሶቹን ጀምሮ በማጠናቀቅ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ።