ማሻ ፣ የመጋቢት 10፣ 2017 (ማሻ ኤፍ ኤም ) ሶስተኛው የአፍሪካ ማዕድን ፎረም በአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
ፎረሙ የሚካሄደው “የአፍሪካ የማዕድን ራዕይ ስኬቶች፣ ፈተናዎች እና እድሎች” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ልዩ ኤጀንሲ የሆነው የአፍሪካ ማዕድናት ልማት ማዕከል ፎረሙን አዘጋጅቷል።
ፎረሙ በማዕድን አስተዳደር፣ እሴት መጨመር እና ዘላቂነት ላይ የሚታዩ መዋቅራዊ እክሎችን መፍታት እና እድሎችን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ከአፍሪካ ህብረት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ባህላዊ የማዕድን ማውጣት ዘዴን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መተካት፣ ወደ ከባቢ አየር የሚገባ የካርቦን ልቀትን መቀነስ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማምጣት የሚያስችሉ መንገዶች ላይም ውይይት እንደሚደረግ አመልክቷል።
በማዕድን መስክ ያሉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የትኩረት መስኮችን ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና አጀንዳ 2063 ጋር አጣጥሞ በማስኬድ ጠንካራ አጋርነት መፍጠር ሌላኛው የፎረሙ አጀንዳ ነው።
የማዕድን ሀብት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ትኩረት የሚሹ የህብረተስብ ክፍሎችን አቅም መገንባት እና ድምጻቸው እንዲሰማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
በፎረሙ ላይ የህብረቱ አባል ሀገራት፣ የማዕድን ዘርፍ ተዋንያን፣ የልማት አጋሮች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።
ፎረሙ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።
ኢዜአ
More Stories
በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ የአቮካዶ ምርቶች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ እያደረጓት ነው
ከወጪ ንግድ 607 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ
በጅማ ዞን የተመረተ ከ6.7 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የአቮካዶ እና የሙዝ ምርት ለገበያ ቀረበ