ዛሬ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች ለዘመናት የተከማቹና ሲንከባለሉ የመጡ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የመሬትና የሀብት ተደራሽነትን ጨምሮ ምላሽ ያላገኙ መሰል ጥያቄዎች ውጤት ናቸው።
ችግሮቹ በወቅቱ በሕዝቦች ውይይት የሚፈቱበት እድል ባለመፈጠሩ ዛሬም ድረስ ያለመግባባትና የግጭት መንስኤዎች ሆነዋል።
ሀገራዊ ምክክር የግጭትንና ያለመግባባት መንስኤ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመረዳት፣ ቅራኔዎችን ለማዳመጥ፣ የጋራ ጥቅምን በመለየት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚተገበሩ መፍትሔዎችን ለመፍጠር የሚያግዝ ሂደት ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከሀገር ግንባታና ማንነት ጀምሮ የመንግሥት አወቃቀር፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች፣ ሀይማኖትና ማኅበረሰብ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብት እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በአጀንዳነት ይዞ ሲካሄድ ቆይቷል።
ምክክሩ ያለፈውን ችግር በመሸፈን አድበስብሶ ማለፍ ሳይሆን ሀገርን ባስቀደመ የመደማመጥ መንፈስ ሲካሄድ መቆየቱን ነው ተመካካሪዎች የሚገልጹት፡፡
ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለ ሰላም ሊጸና አይችልም፤ ግጭት የሰውን ሕይወት ይቀጥፋል፣ ልማትና ኢንቨስትመንትን ያሰናክላል፤ መሠረተ ልማት ያወድማል።
በተቃራኒው ሰላምና የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ኢንቨስትመንትን፣ ንግድን፣ ቱሪዝምን፣ ሥራ ፈጠራንና ምርታማነትን ያበረታታል።
ሀገራዊ ምክክሩ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመትከል፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት እንዲሁም ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርና ማኅበራዊ መተማመን ቁልፍ ሒደት ነው።
ምክክሩ ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከማጥፋት ባለፈ ግጭትን የሚፈጥሩ አለመግባባቶችን የሚያክም የመፍትሔ ባህልን ወደማኖር የሚያሸጋግር ነው።
ይህም ለዘላቂ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለብሔራዊ አንድነት ጠንካራ መሠረት በመጣል የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የሚያስችል ታሪካዊ እድል ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ በእውነተኛ የዜጎች ተሳትፎ፣ በግልጽነትና በመተማመን የሀገር ዘላቂ ጥቅም የተንጸባረቀበት ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
የሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የአንድ ወቅት የፖለቲካ ሂደት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ሰላም፣ አንድነትና ልማት መሰረት የሚጥል ነው፡፡
More Stories
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመዝጊያ መርሀ ግብር
ወቅታዊ መረጃዎችን፣ አስተማሪና አዝናኝ ኘሮግራምችን ተደረሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዛውንቶች የሚገደሉበትና ንብረት የሚዘረፍበት ተግባር የትግል ዓላማ ሊሆን አይችልም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)