May 4, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቴፒ ግቢ  አዘጋጅነት የተካሄደው14ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ተጠናቀቀ ።

”ለዘላቂ ኢንዱስትሪ ፣ኃይል ፣ አካባቢ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሳይንስ እና የምህንድስና መፍትሔዎችን ማሳደግ” በሚል መሪ ሀሳብ በቴፒ ካምፓስ ሲካሄድ የቆየው የምርምር ጉባኤ ተቋጭቷል።

የዩኒቨርስቲው  የምርምር ና አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ግርማ ጥላሁን እንደተናገሩት እስከአሁን የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ከ15 በላይ የምርምር ጉባኤ ማዘጋጀት መቻሉን ተናግረው በጤና፣ ግብርናና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት ማድረጉን አስታውቀዋል ።

በሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤው የሚገኙ ውጤቶች በቀጣይ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ለመንግስት የፖሊሲ አማራጮችን ለማመላከት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቴፒ ግቢ ዋና ስራ አስፈፃሚ እንጂነር መንግስቱ ከተማ አለማችንን እየፈተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ ኢነርጂ መሆኑን ገልፀው  በዚህም በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን፣በኢነርጂ እና አካባቢ ጥበቃ ላይ በጉባኤው የምርምር ስራዎች ቀርበዋል ብለዋል።

ጉባኤው ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማሳደግ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልፀው የምርምር ጹሑፎችም የአካባቢውን ፀጋዎች ማለትም የእንሰት ምርት፣የጨሞ መጠጥ አሰራርና የደን አጠባበቅን ያካተቱ መሆኑን አንስተዋል።

ከጉባኤው  ጉን ለጉን የማህበረሰቡን ባህልና ወግ ለማስተዋወቅ የሸካ፣ማጃንግ እና የሸኮ ባህላዊ የምግብ አሰራር ኢግዚቢሽን የቀረበ ሲሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችም ቀርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት ረገድ የተሳካ እንደነበር ገልፀው ሀገር በቀል ባህልን የማሳደግ እንዲሁም የፈጠራ ሀሳቦች የተንፀባሩቁበትና ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ የምርምር ስራዎች የቀረቡበት ነው ብለዋል።

ሳይንስን ከቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ስራ በመስራት ወደ ማህበረሰቡ ለማውረድ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ጠይቀዋል ።

በመጨረሻም ለጉባኤው መሳካት አስተዋፆ ላበረከቱት አካላት እና ከቀረቡት የምርምር ስራዎችን መካከል ለተመረጡት የዕውቅና ሴርትፍኬት በመስጠት ተጠናቋል ።