የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በዛሬው ዕለት የላይቤሪያ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ብርጋዲየር ጄኔራል ጄራልዲን ጃኔት ጆርጅን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ወቅት ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆናቸውን አስታውሰው፣ ይህ የታሪክ ትሥሥር አሁን ላለው ወታደራዊ ትብብር ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በወታደራዊ ኢንዱስትሪ እና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የላይቤሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ብርጋዲየር ጄኔራል ጄራልዲን ጃኔት ጆርጅ በበኩላቸው፣ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው፣ ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ስምሪትን ጨምሮ በወታደራዊ ሳይንስ እና በዘመናዊ መከላከያ ግንባታ ያካበተችው ተሞክሮ ለላይቤሪያ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት መሆኑን ገልጸዋል።
ላይቤሪያ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰፊ ልምድ የመቅሰም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተለይም በሥልጠና እና በቴክኒክ ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ማስታወቃቸውን የመከላከያ የኦንላይን ሚዲያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ይህ የሚኒስትሮች የሁለትዮሽ ውይይት፣ የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኒዩማ ቦአካይ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አካል ነው።
More Stories
የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ዳግም ያረጋገጡ አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች…
በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ ያገኛሉ ተባለ
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከኢራን ጋር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ