በቅርቡ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ ንረት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ረጅም ወራትን ሊወስድ እንደሚችል የዘርፉ ተንታኞች ገልጸዋል።
በግጭቱ ሳቢያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው የሆርሙዝ ሰርጥ ለትራንስፖርት ምቹ አለመሆን በዓለም አቀፍ የኃይል ገበያ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል ፈጥሯል።
ከአልጀዚራ የተገኘው ትንታኔ እንደሚያሳየው፣ ቀደም ሲል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ይተላለፉበት የነበረው ይህ ወሳኝ የንግድ መስመር፣ የተኩስ አቁሙ ከታወጀ በኋላም ቢሆን እጅግ አነስተኛ መርከቦችን ብቻ እያስተናገደ ይገኛል።
የፍሌቸር ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ሮክፎርድ ዌይትዝ እና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ የገበያ መረጋጋት እንዲፈጠር በባሕረ ሰላጤው በኩል የሚደረገው የጭነት ዝውውር ወጥ እና አስተማማኝ መሆን ይኖርበታል።
ይህ በአንድ ጀምበር የሚሳካ ባለመሆኑ፣ የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ በፍጥነት ወደ ቦታው እንዲመለስ በአሜሪካ፣ ሩሲያ ቻይና እና በቀጠናው ሀገራት መካከል ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ቅንጅት ትብብር እጅግ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎቹ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ሆኖም በሂደቱ ላይ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውንም የአልጀዚራ መረጃ ያመላክታል። እንደ ኢራቅ ያሉ ሀገራት በውጥረቱ ምክንያት ቀንሶ የነበረውን የነዳጅ ምርት በሙሉ አቅም ወደ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እያደረጉ ነው።
የተኩስ አቁሙ ዘላቂ ሆኖ ከቀጠለ የተከማቹ የነዳጅ ምርቶች ወደ ገበያ ሊገቡ እንደሚችሉ መጠበቁ ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ጉዳይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የወደሙ መሰረተ ልማቶች ጥገና መጠናቀቅ እና የመርከቦች የመድን ዋስትና ክፍያ መረጋጋት ለረጅም ጊዜ የዋጋ ቅናሽ መሠረት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የተፈጠረው ቀውስ የዓለምን የኢኮኖሚ ዕድገት ሊገታ እንደሚችል ስጋቱን የገለጸ ሲሆን፣ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የዋጋ ንረቱ ቀዳሚ ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ይህ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነዳጅ አስመጪ ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ስለሚፈጥር፣ የኃይል አቅርቦት እና የነዳጅ ዋጋ ወደ ቀድሞው ዝቅተኛ ደረጃ እስኪመለስ ሁኔታውን ታሳቢ አድርጎ የነዳጅ አጠቃቀሙን ማስተካከል አስፈላጊ ነው።
ዜጎች በነዳጅ እና በተያያዥ የፍጆታ ዕቃዎች አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቁጠባ እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ገበያ ሁኔታ በመገንዘብ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁም ይመከራል።
More Stories
ኢራን እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምታደርሰው ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ትርጉም አልባ ያደርገዋል አለች
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያገለገሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ በማረፋቸው የተሰማኝን ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዓመታዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ገመገሙ