በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውና ዘመናዊ አሠራሮችን የያዘው “መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል፣ በመጋቢት ወር መጨረሻ የመጀመሪያ ዙር አገልግሎቱን እንደሚጀምር ተጠቆመ።
የክልሉና የካፋ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የማዕከሉን የግንባታ ሂደት በቦታው ተገኝተው የጎበኙ ሲሆን፣ በጉብኝቱም የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተክለዓብ ቡሎ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ማዕከሉ በካፋ ዞንና በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ 39 የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣራ ስር ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር 28 አገልግሎቶችን ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁ በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።
የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተክለዓብ ቡሎ ስለ ማዕከሉ ገለጻ ሲያደርጉ እንደገለጹት፣ ግንባታው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረገ ነው። ማዕከሉ የዩኒቨርሳል አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ጨምሮ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence – AI) ማዕከልና ሌሎች ዲጂታል አሠራሮችን በውስጡ ማካተቱንም ከንቲባው አብራርተዋል። ይህም ለአካባቢው ነዋሪዎች አዲስና ቀልጣፋ የሥራ ባሕል ይዞ እንደሚመጣ ታምኖበታል።
የግንባታ ሂደቱን የተመለከቱት አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ ማዕከሉ በተለይም በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የዜጎችን እርካታ ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። በመሆኑም በግንባታው ላይ የሚሳተፉ አካላት ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም፣ የፈጠራ ሥራዎችን በማካተትና በፍጥነት ወደ ሙሉ አገልግሎት እንዲገቡ በአጽንኦት አሳስበዋል።
የማዕከሉ ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የ24 ሰዓት የሥራ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል። ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር የሕዝቡን እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነ
More Stories
በቴፒ ከተማ ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የመሶብ አንድ ማዕከል ከእንግልትና ከምልልስ እንደታደጋቸው ተገልጋዮች ተናገሩ
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፡- በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ወል ትርክትን የመገንባት ጉዞ
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስራ ስኬታማነት ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ተባለ