March 29, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማውን ውብና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ ለበርካቶች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተገለፀ

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማውን ውብና ፅዱ ከማድረግ ባለፈ ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎችና በስራው ላይ እያሉ ያነጋገርናቸው አካላት ተናግረዋል።

በከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

የከተማው ነዋሪ አቶ አይናለም በሰጡት አስተያየት ለልማቱ ስራ ህብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈው ከተማዋን ከሌሎች ከተሞች እኩል ተወዳዳሪ እንዲትሆን የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።

ቤታቸውን ጭምር በፈቃደኝነት ለኮሪደር ልማት ስራ ማፍረሳቸውን የተናገሩት አቶ አይናለም ከተማዋ ውብ፣ማራኪና ፅዱ ሆና ማየት የዘወትር ምኞታቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

የከተማው ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል መኳንንት በሰጠው አስተያየት ‎መንግስት ፅዱ ውብና ለኑሮ ተስማሚ ከተሞችን ለመፍጠር የጀመረው የከተማ ኮሪደር ልማት ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው ብሏል።

‎በክልሉ የኮሪደር ልማት ስራ ከሚተገበሩባቸው ከተሞች አንዱ በሆነው ቴፒ ከተማ ኮሪደር ልማት ላይ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውንም ተናግሯል ወጣት ሳሙኤል።

‎አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አንዱ የሆነው የጌንጂ ኮንስትራክሽን ግንባታ ባለሙያ አቶ ፍቅሬ ገብሬ ኮሪደር ልማት ከመጀመሩ አስቀድሞ ባሉት ጊዜያት የግንባታ ስራዎችን በቀላሉ ማግኘት ከባድ የነበረ ቢሆንም  የኮሪደር ልማት ስራ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በተለያዩ ሳይቶች ላይ በመስራት ራሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደር የሚችልበት ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።

‎ሌላኛው የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት  ጌታሰው መልካሙ በበኩሉ በከተማው የኮሪደር ልማት ስራ በመስራት የተሻለ ገቢ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል። 

በቴፒ ከተማ የእማዳርስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ወ/ሮ ደብረወርቅ በቀለ በበኩላቸው የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን ጠቅሳ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በስራ ላይ እያለ ያነጋገርነው ሌላኛው ወጣት ምርኩዜ ክንዱ እንደተናገረው በፊት ስራ ማግኘት ከባድ መሆኑን ጠቅሶ አሁን በከተማው ኮሪደር ልማት ከተጀመረ ወዲህ በቀን ስራ በመሳተፍ የተሻለ ገቢ በማግኘት ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን እያገዘ መሆኑን ገልጿል።

‎የኮሪደር ልማት ስራ የስራ ባህልን እየቀየረ በመሆኑ ሰራተኞች ሰዓት ከመቁጠር ይልቅ የስራ ስኬታቸው ላይ እንድያተኩሩ እያደረገ በመሆኑ ስራውን በአጭር ጊዜ በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውንም በስራ ላይ ያገኘናቸው ወጣቶች ተናግረዋል። ዘገባው የዞኑ መ/ኮ/ጉ/ ነው።