የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በታርጫ አካሂደዋል።
የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ፣በላብራቶሪ እንዲሁም በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በ6 ወራት የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በሪፖርቱ ላይ በክልሉ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አበረታች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን በመረጃ ጥራት፣በአጎበር አጠቃቀምና በመድኃኒት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍቶች በቀጣይ ሊቀረፉ እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
መድረኩን የመሩት የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በጤናው ተቋማት የላብራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል የሁሉም ዘርፎች ትብብርና ቅንጅት እንደሚሻ ገልጸዋል።
ለህብረተሰቡ ጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ስራዎች ላይ የተገኙ ተሞክሮዎችን ማላቅና ጉድለቶችን በማረም ከችግሩ ለመላቀቅ ዝግጁ መሆንና በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
መረጃን በአግባቡ በመሰብሰብ፣ በማጥራትና በመተንተን፤ ተደራሽነት በማሻሻል መረጃን ለውሳኔ ለመጠቀም የዘርፉ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚገባ የቢሮ ኃላፊው አጽንኦት ተሰጥተዋል።
በመጨረሻም በእጃችን ያለው መዋቅር፣ የሰው ኃይል እና ግብዓት አቀናጅቶ በመጠቀም ውጤታማ የሰው ሀብት አመራር ስርዓት መከተል እንደሚገባ ተናግረው የተለያየ ወረርሽኝን ሲከሰት በራስ አቅም ለመከላከል ከወዲሁ መስራት ይገባል ብለዋል።
በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨምሳ በጤናው ሴክተር ላይ የተቀመጡ ስትራቴጂክ ግቦችን ለማሳካት በጥናትና በምርምር በማስደገፍ ጥራት ያለው መረጃን ለማቅረብ የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተቋሙ መረጃዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለውጤታማነቱ በሰው ኃይል፣ በግብዓትና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተቋም ግንባታ ላይ የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።
ለማህበረሰቡ ስጋት የሚሆኑ በወረርሽኝ መልክና በተፈጥሮ አደጋ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የዘርፉ ሰዎችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት በትኩረትና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ ወሰን በአጽንኦት ተናግረዋል።
በመጨረሻም በጥናቱ በተለዩ ጉዳዮችና በውይይቱ በጉድለት የተነሱ ጉዳዮች ቀጣይነት ያለው ስራ በትኩረት እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን ለመረጃ አያያዝ የሚያገለግሉ ኮምፒውተርና የሰርተፍኬት ሽልማት ለዞኖች ተሰጥቷል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።
More Stories
አሜሪካ ለኢራን ፍልሚያ ተጨማሪ 200 ቢሊዮን ዶላር ጠየቀች!
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ዶክተር ካሳ ለ1,447ኛዉ ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሸካ ዞን የፓርቲና የልማት ስራዎች አፈጻጸም እየተገመገመ ነዉ