March 17, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

በክልሉ የብሔረሰቦችን ባህል፣  ቋንቋ እና የጋራ ዕሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ  ተካሂዷል።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሰለ ከበደ የብዝኅ ማንነቶች ባለቤት የሆነችው አገራችንን ወዴ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር ዘርፈ ብዙ ተግባራት በፌደራል መንግስትና በክልሉ መንግስት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ የዴሞክራሲያዊ መግባባት መርሆዎችን የተከተሉ፣ የሀገረ መንግስት ግንባታ ስራዎች፣ አገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትህ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት ሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ተወካዮች በሚያማክሉ አከባቢዎች በማሰባሰብ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች እየተደረጉ እንዳሉም ተናግረዋል።

የብሔረሰቦችን መብት ማስከበር፣ ህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በማድረግ፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የባህል ልዑካን ዝግጅት፣ የክልሉን ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የጋራ ገፅታ ግንታ፣ የምክር ቤቱን የማስፈፀም አቅም መገንባትና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት በምክር ቤቱ የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሀገር በቀል ችግር መፍታት ላይ ፣የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የወሰን ማስከበር ላይ ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባና በክልሉ በባህላዊና በዘመናዊ መልኩ ግጭቶች እንዲፈቱ መሰራቱን የተሻለ ተግባር በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንድቀጥሉና ሁለም ወደ ልማት ገብቶ እንዲሰራ ከተቋማት ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

በስፍራው የተገኙት የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ የክልሉ ብሔረሰቦች በጋራ በመቀናጀት ባህልና እሴቶቻቸውን እንዲያጎለብቱና እንዲያስተዋውቁ በማሰብ የተመሰረተ በመሆኑ የውስጥና የውጭ ችግሮችን ለመፍታት አባላቱ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኬኒና ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሰለ ከበደ የብሔሮች ብሔረሰቦች አንድነት እንዲጠናከርና የጋራ እሴቶች እንዲጎለብቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ችግሮች እንዳይከሰቱ ከተከሰቱም ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተገልጿል።

ሰላም ለአንድ ግለሰብና ለተቋም የሚተው ባለመሆኑ ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግና የሀገር ሽማግሌዎችን በማካተት ሁሉም በቅንጅት ለሰላም መሰራት እንደሚጠበቅም ተመሏክቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።