February 19, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የመንገድ ደህንነት ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ ።

ማሻ፤ የካቲት 12/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የሚዛን -ቴፒ ዩንቨርሲቲ የመንገድ ደህንነትን ማስጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቴፒ ግቢ ሰጥቷል።

በወቅቱ በትራፊክ አደጋዎች ምክንያት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የመንገድ ደህንነት ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ለማስቻል የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በስልጠናው ላይ የሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ ቴፒ ግቢ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉቀን ደምሴ እንደገለፁት የመንገድ ደህንነትን ማስጠበቅ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ድርሻው የጎላ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት አንዱ የመንገድ ደህነት ስራ መሆኑን ገልፀው  የትራፊክ አደጋዎች እንዲቀንሱ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዘርፍ ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች በመንገድ ደህንነት ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ከትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ እየተከሰቱ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲቀንሱ ያስችላል ያሉት ደግሞ በሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ ግኑኝነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር በሱፍቃድ መኮንን ናቸዉ።

የቴፒ ከተማ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እሃዲግ ጌዳ በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊ እንዲሁም ለልማት ስራዎች አደናቃፊ በመሆኑ ስለ ትራፊክ አደጋ አስከፊነት የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የቴፒ ከተማ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት የመንገድ ደህንነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥላሁን ብርሃኑ የስልጠና ሠነድ ያቀረቡ ሲሆን በሠነዱ መነሻም ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

የተሽከርካሪ ደህንነት ላይ ትኩረት አለመስጠት፣ ከመጠን በላይ ማሽከርከር እና መጫን ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ለትራፊክ አደጋዎች መንስኤ በመሆናቸው ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊዎች ናቸው