February 10, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬት ገለልተኛ ሆነው ሊሰሩ ይገባል- ወ/ሮ ቤተልሄም ዳንኤል

ማሻ፤ የካቲት 2/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ሳይወጡ፣ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ማብቃትና መደገፍ እንደሚገባ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው ይህንን የገለጸው “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግና አፈጻጸም” በሚል መሪ ቃል ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚዛን አማን  እያደረገ ባለዉ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

የመድረኩ ዋና ትኩረት የሲቪል ማህበራት በሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና ማጠናከር እና በቅርቡ በሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ግልጽ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሄም ዳንኤል በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል የነበሩ የህግ ማነቆዎችን በመቅረፍ የዜጎችን የመደራጀት መብት የሚያከብርና የሲቪል ማህበራት በልማትና በዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብት አዲስ ህግ በሀገርና በክልል ደረጃ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።

ኃላፊዋ አክለውም፣ ድርጅቶቹ በሰላም ግንባታና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ድርጅቶቹ የተቋቋሙበትን ህዝባዊ አላማ መሰረት አድርገው ህግን ተከትለው እንዲሰሩ ማብቃት ለነገ የማይባል ስራ ነው ብለዋል።

ወይዘሮ ቤተልሄም እንደገለጹት፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሲቪል ማህበራት ሚና የማይተካ ነው። ለዚህም ስኬት ድርጅቶቹ ከማንኛውም ወገንተኝነት ነፃ ሆነው ገለልተኝነታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የህግ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይነህ አሪሞ ፣ ድርጅቶቹ ሊከተሏቸው ስለሚገባ ደንብና መመሪያዎች እያቀረቡ ይገኛሉ።