ማሻ፤ የካቲት 2/2018 ዓ/ም (ማሻ ኤፍ ኤም 103.8) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለ መኮንን በጋራ በመሆን በምዕራብ ኦሞ ዞን በጀሙ ከተማ ለሚገነባው የ2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልሉ ሰፊ የግብርና፣ የእንስሳት ማዕድን ሌሎች ሀብቶች የሚገኝበት አካባቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
በክልሉ በአርብቶ እና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳት ሀብት በስፊው የሚገኝ ቢሆንም ዘመናዊ የእንስሳት ግብይት ማዕከልና ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት ባለመኖሩ ከዘርፉ ብዙ ጥቅም ሳይገኝ መቆየቱንም አስረድተዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በጀሙ ከተማ የሚገነባው የ2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በዘመናዊ መንገድ የቁም እንስሳት ግብይት እንዲከናወን፣ ህገወጥ ደላላዎችን በመከላከል የተሳለጠ የንግድና ግብይት ሰንሰለት እንዲኖር እንዲሁም ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚላከውን የእንስሳት ሀብት ከፍ ለማድረግና በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያስችላልም ብለዋል።
የማዕከሉ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የድጋፍና ክትትሉ እንደሚጠናከርም ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢፊዲሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለ መኮንን በበኩላቸው ሚኒስቴር በምዕራብ ኦሞ ጀሙ ከተማ የሚገነባው የ2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከሉ በ74 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚገነባና በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው አከባቢው ሰፊ የእንስሳት ሀብት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው የሚገነባው ዘመናዊ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲናገኝ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። ዘገባው የክልሉ መ/ኮ ነው።
More Stories
ውስጣዊ ሰላምን ማፅናት፦ ወቅቱ የሚጠይቀው አርበኝነት
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በካፋ ዞን የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ
ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት በ68 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባዉን የባቹማ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተመረቀ