በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
የዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ተፋላሚ ብሔራዊ ቡድኖችን የለየ ሲሆን ÷ በዚህም ስፔን እና አርጀንቲና ለዋንጫው ይፋለማሉ፡፡
ስፔን ለዋንጫ የተገመተችውን ሌላኛዋን ሀገር ፈረንሳይን በግማሽ ፍጻሜው 2 ለ 0 በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኗ ይታወሳል፡፡
በአሰልጣኝ ሉዊስ ዴላፎንቴ የምትመራው ስፔን እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 13 ግቦችን አስቆጥራለች፤ የተቆጠረባት ደግሞ አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡
ስፔን በፈረንጆቹ 2010 የዓለም ዋንጫን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳካች ሲሆን÷ በድጋሚ በመድረኩ ለመንገስ በፍጻሜው ከአርጀንቲና ጋር ትፋለማለች፡፡
ተጋጣሚዋ ሀገር አርጀንቲና ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው እንግሊዝን 2 ለ 1 በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆናለች፡፡
በጨዋታው እንግሊዝ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ ብትሆንም አርጀንቲና ከመመራት ተነስታ በማሸነፍ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መድረክ ፍጻሜ ላይ ተገኝታለች፡፡
አርጀንቲና እስካሁን ድረስ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቿ ላይ 19 ግቦችን ያስቆጠረች ሲሆን÷ 7 ግቦችን ደግሞ አስተናግዳለች፡፡
በ2022 የዓለም ዋንጫን ያሳካችው አርጀንቲና በተከታታይ ዋንጫውን ለማሳካት የምታደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
ስፔን በታሪኳ ለ2ኛ ጊዜ እንዲሁም አርጀንቲና ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማሳካት የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
የ2026 የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የፊታችን እሑድ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይደረጋል፡፡
በፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ተሸንፈው ጉዟቸው የተገታው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ደግሞ ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
More Stories
እንግሊዝ ከኖርዌይ፤ አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ …
ስፔን ቤልጂየምን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈች
ሪያል ማድሪድ የዓለማችን ውዱ ክለብ ሆነ