July 15, 2026

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የክልሉ ወጪዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል የገቢ አሰባሰብ አቅም እየተፈጠረ ነው፦ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ለ’ እና ‘ሀ’ ግብር ማስጀመሪያ የንቅናቄ “ለክልላችን ልማት ግብርን በታማኝነት!” በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ባለፋት አምስት ዓመታት በክልሉ የገቢ አሰባሰብ እያደገና እየተሻሻለ መምጣቱንና በዚህም የክልሉን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መኾኑን ነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገለጹት።

ክልሉ አሁንም ቢሆን ጥቅም ላይ ያልዋለ እምቅ የገቢ አቅም እንዳለው የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በቀጣይም ገቢን በተሻለ እና ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመሰብሰብ የሚያስችል ክልላዊና አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መኖራቸውን በዝርዝር ገልጸዋል።

በየጊዜው እያደገ የመጣውን የህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት እና የመንግሥትን ወጪዎች ለመሸፈን ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኝነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የገቢ ግመታ ተግባር ሙያዊ ብቃትን የተላበሰ፣ ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት የሰፈነበት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡት ዶ/ር ነጋሽ በዚህ ሂደት ውስጥ የገቢ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቀው እንዲሰሩና የተጠያቂነት ስርዓት ሊሰፍን እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ከግብር ከፋይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በየደረጃው ተቀብሎ በአግባቡ መፍታት እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ክልላዊ የገቢ አሰባሰብ ማነቆዎች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የክልሉ የገቢ አሰባሰብ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን የገለጹት የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ፤ ክልሉ ሲመሰረት ከነበረበት 3.2 ቢሊዮን ብር የገቢ ድርሻ (36 በመቶ) በመነሳት፣ በ2018 በጀት ዓመት ከ18.091 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

ይህ አፈጻጸም የዕቅዱን 98.21 በመቶ ያሳካ ሲሆን፣ የክልሉን መንግሥት ዓመታዊ የልማት ወጪ 64.5 በመቶ ያህሉን በራስ አቅም ለመሸፈን ትልቅ አቅም መፍጠሩን አብራርተዋል።

ቢሮው የታክስ ስርዓቱን ለማዘመንና ከእጅ ንክኪ የጸዳ ለማድረግ ባደረገው ጥረት፣ በሁሉም 70 የታክስ ማዕከላት የሲግታክስ (SIGTAS) ሲስተም እንዲዘረጋ በማድረግ ግብር ከፋዩ ጊዜና ወጪውን ቆጥቦ በቴሌብርና በባንክ በኢ-ታክስ አማካኝነት ግብሩን የሚከፍልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ፣ ደረሰኝ በማይሰጡ 272 ግብር ከፋዮች ላይ በተደረገ ኦፕሬሽን ከ22.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ያሉት ሀላፊዋ።

እንዲሁም በስጋት መስፈርት 555 ግብር ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ ከታቀደው 217 ሚሊዮን ብር በላይ በማለፍ 286.1 ሚሊዮን ብር ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የስነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 50 የተቋሙ ባለሙያዎች ላይ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ እስር የሚደርስ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በመድረኩ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የገቢ ተቋም ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

ክ/መ/ኮ